የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትጋት እንሰራለን

61

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 1/2014(ኢዜአ) ባለፉት ዓመታት በዞኑ ህዝብ ሲነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትጋት እንሰራለን ሲሉ በጋምቤላ ክልል የኑዌር ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቦት ቴር ተናገሩ።
የዞኑ ምክር ቤት ባካሄደው ስድሰተኛው  የምርጫ ጊዜ አንደኛ  የስራ ዘመን መስራች ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን አጸድቋል።

በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ በተካሄደው መስራች ጉባኤ የተሾሙት የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ቦት ቴር ቃለ መሃለ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ በቀጣይ አምስት ዓመት የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን  አጠናከረው በማስቀጠል የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በዞኑ ህዝብ ሲነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትጋት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

መስራች ጉባኤ በነበረው የአንድ ቆይታ ወይዘሮ ኛኮት ቦል የብሔረሰብ ዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፤ ወይዘሮ ቾል ሉክን ደግሞ ምክትል አፈ -ባኤ አደርጎ ሾሟል።

ከዚህም ሌላ  አቶ ጆን ቾልን ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ፤ እንዲሁም  21 የዞን ካቢኔ አባላት ሹመትንም መስራች ጉባኤው መርምሮ አጽድቋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና ኮንስትራኮሽ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተንኳይ ጆክ ፤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሙስና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል የዘኑን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አዲሶቹ አመራሮች ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተለይም ዞኑ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ድንበር ዘላል የጸጥታ ችግሮች በመከላከል ረገድ በላቀ ቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም