በኢትዮጵያ ተቋማት ላይ በ2013 ዓ/ም 2 ሺህ 800 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል

75

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት /2014 (ኢዜአ) በ2013 ዓ/ም በኢትዮጵያ  ተቋማት ላይ   2 ሺህ 800 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ተናገሩ።

የሳይበር ደህንነትን ማወቅና በዘርፉ ሊከሰት የሚችልን ጥቃት መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
 በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ/ም የሚቆየው የሳይበር ደህንነት ወር  "የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃለፊነት፤ እንወቅ እንጠንቀቅ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ መከበር ጀምሯል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በዚህን ወቅት በሳይበር ደህንነነት ላይ በቂ ግንዛቤ ተይዞ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካልተደረገ በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት መከናወኗ፣ አገራዊ ምርጫ ማካሄዷንና ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ህግ የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን  ጠቁመዋል።

ለአብነትም በኢትዮጵያ በ2013 ዓ/ም ብቻ በተለያዩ ተቋማት 2 ሺህ 800 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የሳይበር በይነ መረብ ቴክኖሎጂ ይዞት የመጣውን የእድገት አማራጭ መጠቀምና በዘርፉ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት መቋቋም እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው "ለሳይበር ጥቃትና ደህንነት በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ካልተቻለ በተቋማት ብሎም በሀገር ላይ አስከፊ አደጋ ሊከሰት ይችላል" ብለዋል።

በመሆኑም የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ብቁ የሰው ኃይል፣ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እና በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ  በሳይበር ጥቃት 2 ነጥብ 5 ትርሊየን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ መድረሱን ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን፤ በ2021 ደግሞ 6 ትርሊየን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል።

የሳይበር ደህንነነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም