የጎንደር ከተማና አካባቢውን ሰላም ሊያውክ በሚችል እንቅስቃሴ የሚሳተፉ አካላት ላይ ክትትል እየተደረገ ነው

53

መስከረም 30 /2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማና አካባቢውን ሰላም ሊያውክ በሚችል እንቅስቃሴ የሚሳተፉ አካላት ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የጎንደር ከተማና አካባቢውን የተሟላ ጸጥታ ለማስቀጠል ህዝብን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የህዝቡን ሰላም ሊያውክ የሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የከተማው ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ አስታውቀዋል።

ማንኛውንም ጸረ-ሰላም እንቅስቃሴ የመከላከል ቅንጅታዊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ሦስት ወራት በግልና በቡድን መዋቅር ዘርግተው በከተማው የጥፋት ተልእኮ ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተገኙ የጥፋት ሃይሎች ከነተባባሪዎቻቸው ጋር መያዛቸውን ተናግረዋል።

ከነዚህ ውስጥም አሸባሪው ህወሃት በክልሉ ወረራ መፈፀም በጀመረ ማግስት የሽብር ተግባር እንዲፈጽሙ ወደ ከተማው አስርጎ ያስገባቸው እንዳሉበት ገልፀዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የሽብር ተግባር ፈጻሚዎች መካከል በባህር ዳርና አዲስ አበባ ጭምር መዋቅር ዘርግተው የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን በምርመራ ማረጋገጥ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በዚህም በከተማው ሊፈፀሙ የነበረውን የሽብር ሙከራዎች በህዝቡ ጥቆማና ትብብር ማክሸፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተው የሰው ማገት ወንጀል ድብቅ የፖለቲካ አላማ ባላቸውና የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ ወንጀለኞች የተፈፀመ መሆኑንም ኮማንደር አየልኝ አብራርተዋል፡፡

በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ 18 ያህል የሰው እገታ ወንጀል መፈጸሙን አስታውሰው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተሳትፎ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 28 ሰዎች በፖሊስ ቍጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

“የሰው እገታ ወንጀል መፈፀማቸው የተረጋገጠባቸው ሌሎች 17 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ለጊዜው በመሰወራቸው ፖሊስ የማደኛ ትእዛዝ አውጥቶ የተጠናከረ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

በከተማው በህገ-ወጥ መንገድ መሳሪያ በመተኮስ የከተማውን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ የጣሉ 104 የመንግስትና የግል ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለው ከ275 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍሉ መደረጉንም አስረድተዋል።

ስምሪት ከተሰጣቸው አካላት ውጪ በከተማው በግልም ይሁን በቡድን የጦር መሳሪያ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስን ለማስቆም እና በቴሌ፣ መብራትና መሰል መሰረተ ልማት የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችን ለማስቆም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ገልፀዋል።

የከተማውን የቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የተሳለጠ በማድረግ ፖሊስ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሃላፊው አስታውቀዋል።

የፖሊስን የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን አባላት በመለየትም እርምጃ ለመወስድ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም