የቱሪዝም መስህቦችን የማስተዋወቅ ዓላማ የያዘ የጎዳና ላይ ሩጫ በባሌ ሮቤ ተካሄደ

73

መስከረም 30 / 2014 (ኢዜአ) የቱሪዝም መስህቦችን የማማስተዋወ ዓላማ ያለው የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ተካሄደ።

'መንገዶች ሁሉ ወደ ባሌ' በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የሩጫ ውድድሩ አትሌቶችን ጨምሮ ከ3 ሺህ በላይ ተሳታፊ ነበረው።

ውድድሩ የተዘጋጀው በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና በሳዲያ መልቲ ሚዲያ ትብብር ሲሆን የ2014 ዓ.ም 'ወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ' የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ ሃሊማ አብዱልሸኩርን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ታድመዋል።

ውድድሩን ያስጀመሩት የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ እንዳሉት፤ በበርካታ የቱሪዝም መስህብነቷ የምትታወቀውን ባሌ የቱሪዝም መስህብ በተለያየ መንገድ ማስተዋወቅ የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያነቃቃል።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ተወካይ አቶ ፍጹም ካሳሁን በበኩላቸው "የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል" ብለዋል።

በዞኑ ለ3ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫም የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም