በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተነገረ

74
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታወቀ። የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ፈረደ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የተፈጠረው የሥራ ዕድል በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና በመንግስት መዋቅር በተደረገ ቅጥር ነው። በጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ 1 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል። በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና በመንግስት መዋቅር ውስጥ 600 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 66 ነጥብ 7 በመቶ በቋሚነት 33 በመቶ ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፈጠሩን አቶ አሰፋ ተናግረዋል። ከስራ ዕድሉ ተጠቃሚዎቹ ውስጥ 416 ሺህ 488 ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። አካል ጉዳተኞች፣ ከስደት ተመላሾች፣ የዩኒቨርስቲና የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች ከሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው አመልክተዋል።  ኤጀንሲው ለ 1 ሚሊዮን ወጣቶች ገበያ ተኮር አጫጭር ስልጠና ለመስጠት አቅዶ ለ810 ሺህ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።  እንዲሁም ለ225 ሺህ 896 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መሰጠቱን አስታውቀዋል።  በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከታቀፉ አዲስ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ 40 ሺህ 142 የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች መከናወኑን ገልጸዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የገበያ ትስስር ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ብቃት ማነስ፣ የምርት ጥራት ጉድለትና የብድር አቅርቦት ችግሮች እንዳጋጠሙ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም