በጥበብ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በማንኛውም ግዳጅ ለመሰለፍ ተዘጋጅተዋል

116

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014 (ኢዜአ)  በጥበብ አማካኝነት ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በማንኛውም ግዳጅ ለመሰለፍ መዘጋጀታቸውን የማርቺንግ ባንድና ኦርኬስትራ ምሩቃን ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በማርቺንግ ባንድ፣ ኦርኬስትራና ቴአትር ሙያ ያሰለጠናቸውን 128 የፖሊስ አባላት ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች እንደገለጹት፤ በሥልጠና ወቅት ሙያዊ ስነ-ምግባር በመላበስ አገርና ህዝብን ለማገልገል የሚያስችላቸውን የንድፈ ሃሳብና የተግባር እውቀት ቀስመዋል።

በአዲስ አበባ ወንጀል ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤና ጥንቃቄ መልእክቶችን በማስተላለፍ በሙያቸው አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጥበብ አማካኝነት የወንጀል መከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር "የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በማንኛውም ግዳጅ ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል" በማለት ነው ያረጋገጡት።

የኮሚሽኑ ሙዚቃና ትያትር ማስተባበሪያ ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እንዳልካቸው ታደሰ፤ ኢትዮጵያ ለገባችበት የህልውና ዘመቻ ግንባር ድረስ በመሄድ ሙያዊና ሌሎች ግዴታዎች ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለሰልጣኞቹ የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ተመራቂዎች ቀጣይ በሚኖራቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በፖሊሳዊ ስነ-ምግባር ስራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

ኮሚሽኑ ረዥም ታሪክ ያለው ቢሆንም የራሱ የሆነ የሙዚቃ፣ ቲያትርና የማርቺንግ ባንድ እንዳልነበረው አውስተው፤ ተቋማዊ ለውጡ ሲደረግ መደራጀቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ጌቱ እንደገለጹት፤ ተመራቂዎቹ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ተግባር ደጋፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማፍራት የግንዛቤና ጥንቃቄ መልክቶችን የማስተላለፍ ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው።

የተቋሙን ገጽታ ለመገንባትና ህብረተሰቡ ለጸጥታ ስራ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ለከተማዋ የሚመጥን የፖሊስ ሃይል ለመገንባትና በሰራዊቱ ውስጥ የስራ መነቃቃት ለመፍጠር የማርቺንግ ባንድ፣ የሙዚቃና ቲያትር ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ተመስርቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ የግልና መንግስታዊ ተቋማት የምስጋና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም