ተመራቂዎች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር መንግስትን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል

132

አዳማ ፤ መስከረም 29/2014(ኢዜአ) ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር መንግስትን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ አስታወቁ።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 3ሺህ 490 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት  አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ ባደረጉት ንግግር “ህዝቡ አሁን ከኛ ወሬ ሳይሆን ተጨባጭ ለውጥ አምጥተን ማየት ነው የሚጠብቀው ” ብለዋል።

ተማሪዎች በቆይታቸው ያገኙትን ክህሎትና ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር መንግስትን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ሌብነትና ብልሹ አሰራር ያለምንም ማመንታት መታገል፤ የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተንዛዛ አሰራር እንዲወገድ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ሀገራችን አሁን ከገባችበት ችግር በማላቀቅ ወደ አዲስ ምዕራፍና ከፍታ መውሰድ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና  የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው፤  ዩኒቨርስቲው ከኦሮሚያ አልፎ የአጎራባች ክልሎች የሰው ሃይል የማስፈፀም አቅም ግንባታ በግንባር ቀደምትነት በማገዝ ረገድ የያዘውን አቅጣጫ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሀገራችን ጠንካራ መንግስት ከመመስረቱም በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያካተተ የካቢኔ አባላት በማደራጀት ጠላት አንገቱን የደፋበት ማግስት መሆኑ ምርቃቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ተማሪዎች ባገኙት ዕውቀት፣ ክህሎትና ሙያ ዴሞክራሲና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መረባረብ ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሀገራችን ባለብዙ ማንነት፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል ባለቤት መሆንዋን በተግባር በማረጋገጥ ረገድ ዩኒቨርሲቲው አሁንም በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።


በዚህም አብሮ መልማት፣ ማደግ፣ መበልጸግ እንድንችል የተማርነውን ትምህርትና ያገኘነውን ዕውቀት በአግባቡ ልንጠቀምበትና የሀገራችን ችግሮች መፍታት አለብን ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሲቪል ሠራተኞች የማስፈፀም አቅም ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

ወቅቱ የሚፈልገውን አቅም ለመፈጠር፣ የአመራር ልማትና ሀገሪቱ ለያዘችው የመዋቅራዊ ሽግግር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠርም እንዲሁ።

ተቋሙ 11 የጥናትና ምርምር ማዕከላትን በስሩ በማደራጀት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማነት ላይ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የሚችሉ 107 የጥናትና ምርምር ስራዎች በማከናወን ለመንግሥት ማስረከቡን ያመለከቱት ዶክተር ገመቹ፤  በ20 የክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች የአሰራር ውጤታማነት ላይ ጥናት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

አሁንም በ10 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ የፕላንና ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ጥናት እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለጋምቤላና ሱማሌ ክልሎች በተለያዩ ፕሮግራሞች የትምህርት ዕድል በመስጠት የክልሎችን የሰው ሃይል የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት  እያገዘ ይገኛል።

ተመራቂዎች በበኩላቸው በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ ልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በ17 የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 1ሺህ 190 ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም