ኢትዮጵያዊያን ለሠላም በቁርጠኝነት ከቆምን ፈተናዎችን አልፈን ታላቅ አገር እንገነባለን

76

አዲስ አበባ፣  መስከረም 29/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በመሉ ለሠላም በቁርጠኝነት ከቆምን ፈተናዎችን አልፈን ታላቅ አገር እንገነባለን ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ተማሪዎች በርካታ አስቸጋሪ ወቅቶችን በማለፍ ለዛሬው ምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

የትምህርት ዘርፉ አገር ከዚህ አስቸጋሪ ወቅት ወጥታ በጀመረችው የለውጥ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ የሚያደርጉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የማፍራት ታላቅ ኋላፊነት ተጥሎበታልም ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች አገራቸውን የሚወዱ፣ በሙያቸው ጠንካራ የሆኑ እና በስነ-ምግባርም የታነጹ እንዲሁም የአገርን ክብር የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

"በአሁኑ ወቅት በአገራችን ብዙ ፈተናዎችን ስላየን ከዚህም ብዙ ትምህርቶችን መውሰድ ያስፈልጋል" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አዲሱ ትውልድ ለውጥ አምጪ እንጂ የታሪክ ስህተቶችን መድገም እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ 

ተመራቂዎች ሁሉንም ሰው በእኩልነት ማክበርና ማገልገል ይገባልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሁሉም ዜጎች በያሉበት ሁሉ ለሰላም ዘብ በመቆም አገራቸውን ከችግር ማውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አሁንም ለሰላም መከበር ሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች ከአገር ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በማህበራዊ አገልግሎት ተግባር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ በጥቁር አንበሣ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ የሚገኘውን የነጻ የህክምና አገልግሎትን አድንቀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት በተለያዩ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 6 ሺ 163 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም