አለም አቀፍ ጫና ይዞት የሚመጣውን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ለመቋቋም በህብረት መቆም ያስፈልጋል- ምሁራን

68

ሀዋሳ፤ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) አለም አቀፍ ጫና ይዞት የሚመጣውን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ለመቋቋም በህብረት በመቆም የልማት ስራዎች ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ።

በወቅታዊ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራን  አሜሪካን ጨምሮ የአንዳንድ  ምዕራባዊያን ሀገራት መንግስትን ለማዳከም የመንቀሳቀስ ምክንያት የህዝቡን ስነ ልቦና መጉዳት ዋነኛ ስልታቸው ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳጋላ ኤርጋኖ፤ ኃያላን ሀገራት ምጣኔ ሀብታቸውን  ማሳደግ በመቻላቸው በአለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን መቻላቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቋቋም ምጣኔ ሀብትን ሊያሳድጉ በሚችሉ  የልማት ስራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሀገራቱ ማዕቀብ መጣልን እንደ መጀመሪያ አማራጭ አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ያስረዱት ምሁሩ፤ ይህንን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል እንቅስቃሴ ከማድረግ ባለፈ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።  

በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እየተፈጸመ ያለውን የንግድ አሻጥሮችን ሥርዓት በማስያዝ የዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ቀዳሚ ስራ  ሊሆን እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚው እንዳይዋዥቅም የተጀመረውን የዘርፉ ሪፎርም በትክክለኛ መሰረት ላይ በማቆም የኃያላን ሀገራትን ሴራና ጫና መመከትም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ያለንን ውሰን መሬትና ሀብት በማቀናጀት ምርታማነትን ለማሳደግ መትጋት ከአምራች አርሶ አደሩና ከዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።   

ዜጎችና መንግስት ከተባበሩ ምጣኔ ሀብትን በፍጥነት ማሳደግ እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር ዳጋላ፤ ለሀገር በቀል እውቀት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

በዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አወል ዓሊ፤ ያደጉ ሀገራት በዓለም ላይ ተሰሚነትና ተቀባይነት እንዳላቸው ተናግረዋል። 

በአንፃሩ አፍሪካዊያን የተፈጥሮ ፀጋ ሳያንሳቸው በእርስ በእርስ ጦርነት፣ ደካማ የስራ ባህል እና በሌሎችም ተፅዕኖዎች ምክንያት ለድህነት በመዳረጋቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ ከውጭ  ጫና  ለመላቀቅ ከምን ጊዜውም በላይ  ወጣቱን ኃይል በማንቀሳቀስ ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት እና ግንባታቸው የተጀመሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በማድረግ በርካታ  ዜጎችን የስራ እድል  ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አሁን ላይ በህዝብና መንግስት መካከል እየታየ ያለውን መተባበርና መደማመጥ የአንድነት ማሰሪያ በማድረግ የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት  ተጽዕኖ መቋቋም  እንደሚቻል ተናግረዋል።

''ያለጠንካራ ህዝብ ጠንካራ መንግስት አይመሰረትም'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አወል አሁን ላይ እየታየ ያለው የመንግስትና የህዝቡ ህብረት በማጠናከር  አለም አቀፍ ጫናዎች  በመቋቋም የአፍሪካዊያን ተምሳሌት መሆን እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

አንዳንድ ምዕራባዊያን በአፍረካ ሀገራት ላይ የሚያሳድሩትን የኒዮ ኮሎኒያሊዝም ተጽዕኖ እንዲያቆሙ ብርቱ ጥረት ማደረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ '' አባቶቻችን አድዋ ላይ የሰሩትን ታሪክ መድገም ይገባል'' ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም