የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ወራት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል

62

ዲላ፤ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወነው ውጤታማ ስራ በበጋ ወራትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ተመለከተ።

በዲላ ከተማ አስተዳደር  በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ አስተዋጾ ላበረከቱ ወጣቶችና  ማህበራት የከተማ አስተዳደሩ እውቅና ሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ  የከተማዋ  አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ዘመናይ ህሪባዬ እንዳሉት በከተማው 7 ሺህ 500 የሚደርሱ ወጣቶች በ11 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ሰጥተዋል።

29 የአረጋዊያን የመኖሪያ ቤት እድሳት፣ የ690 ችግረኛ ህጻናት የመማሪያ ግብዓት ድጋፍ፣ ችግኝ ተከላና ደም ልገሳ በወጣቶቹ  ከተከናወኑ  ስራዎች ይገኙበታል።

በዚህም  4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ስራ መከናወኑን ያመለከቱት ሃላፊዋ፤ በዚህም  ከ24 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ የዲላ ከተማ  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንግስቱ ተክሌ በበኩላቸው፤  ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በነቂስ ከመሳተፍ ባለፈ የአከባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።

በክረምት ወራት የታየው ውጤታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወራትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ወጣቶች በበጋ ወራት ትምህርታቸውን ከመከታተል በተጓዳኝ  ማህበረሰባቸውን  በማገልገል በጎ ተጽዕኗቸውን  ማጉላት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው መካከል የዜዊ በጎ ፍቃድ ማህበር አስተባባሪ ወጣት አቤነዘር ብርሃኑ ፤  የማህበሩ አባላት በአረጋዊያን ቤት እድሳትና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ ህብረተሰቡን ማገልገላቸውን  ተናግሯል።

አገልግሎቱ የማህብረሰቡን ችግር ከማቃለል ባለፈ ለማህበሩ አባላት የህሊና እርካታ ማጎናጸፉን ገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ አስተዋጾ ላበረከቱ 7 የበጎ ፈቃድ ማህበራትና ወጣቶች የእውቅና ሰርተፍኬት የተሰጠ ሲሆን የደም ልገሳ መረሃ ግብር ተካሂዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም