የሴት የሕግ ምሁራን ቁጥር ሊያድግ ይገባል

73

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሴት የሕግ ምሁራን ቁጥር አሁን ካለበት አነስተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ተናገሩ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ሴት የሕግ ተማሪዎች በፍትህ ሥርዓትና በሴቶች ሚና ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር አካሂዷል።

መድረኩ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ3ኛ እስከ 5ኛ ዓመት የሚገኙ ሴት የሕግ ተማሪዎች ከሕግ ባለሙያ ሴቶች ልምድ የሚቀስሙበት ነው።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እንደተናገሩት በመጀመሪያ ዲግሪ የሚመረቁ ሴት የሕግ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል።

ይሁንና በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የሚመረቁ ሴት የሕግ ምሁራን ቁጥር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው ይህ አሃዝ ሊያድግ እንደሚገባ ተናግረዋል።   

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ የሕግ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረው መሰል መርሃ ግብሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

መርሃ ግብሮቹ ዜጎች ስለ ሕግ፣ ስለ ፍርድ ቤቶች አሰራር እንዲሁም ስለ መብትና ግዴታዎቻቸው ግንዛቤያቸው እንዲያድግና በዚያው መሰረት እንዲመሩ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

በተለይም በትምህርት ላይ ያሉና በቀጣይ ዘርፉን የሚቀላቀሉ የሕግ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ከሚያገኙት እውቀት ጎን ለጎን ትክክለኛ አሰራሩን ማወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ሴት ተማሪዎችም በትምህርትና በሥራ ላይ እያጋጠሙ ያሉና ወደፊት ስጋት ይሆናሉ ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች አንስተዋል።

በዘርፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑና የረጅም  ዓመት ልምድ ያላቸው  የሕግ ባለሙያ ሴቶች  ለተማሪዎቹ ልምዳቸውን በማካፈል ለጥያቄዎቻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሴት ሙያተኞች ከነባሮቹ በቂ ልምድ እንዲወስዱ በማድረግ በሥራ ዓለም ለሚያጋጥማቸው ተግዳሮት መፍትሄ አምጪ እንዲሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም