ትምህርት ቤት በአቅራቢያችን መገንባቱ በዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ያግዛል -የባቢሌ አካባቢ ነዋሪዎች

72

ሐረር፤መስከረም 28/2014(ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ የተገነባው የኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘት በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ ።

ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው ትምህርት ቤቱ የኦሮሚያ፣ ሱማሌ እና ሐረሪ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች በተገኙበት ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የባቢሌ ነዋሪዎች፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለዘመናት ጥያቄያቸው መፍትሄ በመስጠቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል ።

ትምህርት ቤቱ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አመልክተው፤ በአቅራቢያቸው ጥራት ያለው ትምህርት ለማገኘት በመታደላቸው ቀጣይ የትምህርት ህይወታቸውን የተቃና እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ተማሪ ሙራድ መሐመድ በሰጠው አስተያየት፤ ይህን የመሰለ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በአቅራቢያችን ይሰራል ብዬ አስቤ አላውቅም ብሏል።

ትምህርት ቤቱ በሚቀጥለው ወር አገልገሎት ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጾ፤ በዚህም በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዛቸውና ጠንክሮ ለመማርም መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የተማሪ ወላጅ ወይዘሮ ኑሪያ ወዚር በበኩላቸው፤ በአካባቢው ትምህርት ቤት እንዲገነባ ስናቀርበው ለነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘታችን አስደስቶናል ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ መገንባት በአቅም ችግር ትምህርታቸውን እያቋረጡ ለሚገኙ ተማሪዎች አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆን ነው የገለጹት ።

በወረዳው አቅራቢያ የሆኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግር በመኖሩ ሴቶች ትምህርት ያቋርጡ እንደነበር ጠቅሰው የትምህርት ቤቱ መገንባት ይህንን ችግር በማቃለል በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ መምህር መሐመድ ኢብራሂም ናቸው።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዱኛ ሁለቃ፤ ዘንድሮ በዞኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በባቢሌ ወረዳ ማዕከላዊ ስፍራ ላይ በመገንባቱ ተጎራባች ከተሞችን ጨምሮ ለ1 ሺህ 500 ተማሪዎች አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በገንዘቡ ፣ ጉልበቱ እና የእርሻ መሬቱን በመስጠት ትምህርት ቤቱ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማደረጉን አስታውቀዋል።

በባቢሌ ወረዳ የተገነባው ትምህርት ቤት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አጋዥ የሆኑ ዘመናዊ ቤተ-ሙከራ፣ ሰርቶ ማሳያ፣ ቤተ-መፃህፍትና ሌሎችም ለመማር ማስተማር ስራ የሚያገለግሉ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም