ተቋማት የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን በሚያስተዳድሩ አካለት ላይ የሙያ ብቃትና የስነ-ምግባር ማጣራት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

110

መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) ተቋማት የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን በሚያስተዳድሩ አካለት ላይ ጥብቅ የሆነ የሙያ ብቃትና የስነ-ምግባር ማጣራት እንዲያደርጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳሰበ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በተቋማት የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮች ደሀንነት ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው “ሀገራችን አሁን እያከናወነችዉ ካለችው የህግ ማስከበርና የህልዉና ዘመቻ ጋር እንዲሁም ሌሎች ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ጠላቶች እና ተባባሪዎቻቸው ከውስጥና ከውጭ ሆነው የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም በተለያዩ የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ሊሳካላቸው አልቻለም” ብሏል፡፡

ነገር ግን አሁን እየታዩ ያሉት አዝማሚያዎችና ሙከራዎቻቸውን ማሳሰብና ማሳውቅ አስፈልጓል ያለው አስተዳደሩ፤ እነዚህ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት እዚሁ ሀገር ዉስጥ ሆነው የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን እንዲያስተዳደሩ በተቋማት መብት የተሰጣቸውን ለሙያቸው፤ ለተቋማቸውና ለሀገራቸው ታማኝ ያልሆኑ ጥቂት ጡት ነካሽ ባንዳዎችን በመጠቀምና እክል ለመፍጠር እየሰሩ ይገኛል ሲልም አስታውቋል፡፡

“ስለሆነም ማንኛዉንም የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን የምታስተዳደሩ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት ሲስተሞችን እንዲያስተዳደሩ መብት የተሰጣቸው ወይም የተቋማትን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲያስተዳድሩ የይለፍ-ቃል እንዲይዙ የተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ትክክለኛውን የሙያ ብቃት እና ጥብቅ የስነ-ምግባር ማጣራት የተደረገባቸው መሆኑን ደግማችሁ፣ ደጋግማችሁ እንድታረጋግጡ እናሳስባለን” ሲል ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም