ሲኤንኤን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያወጣው ዘገባ ተቀባይነት የለውም

125

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሲኤንኤን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያወጣው ዘገባ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያዎችን አጓጉዟል’ በሚል በሲኤንኤን በቅርቡ የወጣው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑ አየር መንገዱ መግለጹን የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበርካታ አለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤት የስታርአሊያንስ አባል በመሆን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም አገሮች አስተማማኝና ቀልጣፋ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ እንደሆነ አስታውሷል።

ላለፉት 75 ዓመታት ያክል በአለም ዙርያ ለበርካታ ሃገራት ለሰብአዊ እና ለንግድ ሥራዎች አገልግሎት በመስጠት የተመሰገነ መሆኑንም አስገንዝቧል።

“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም ብሔራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተዛማጅ ደንቦችን በጥብቅ ያከብራል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ በቅርቡ በሲኤንኤን በኩል የቀረበውን ውንጀላ አጥብቆ ተቃውሟል።

“በማንኛውም ጊዜ የትኛውንም የጦር መሣሪያ በማንኛውም አውሮፕላን አላጓጓዘም” ሲል ገልጿል።

ሲኤንኤን የጦር መሳርያ ተጓጉዟል በሚል በማስረጃነት ያቀረበው ሰነድ እንደተባለው የጦር መሳሪያ ሳይሆን የምግብ ሸቀጥ የተጓጓዘበት እንደሆነ አመልክቷል።

የቀረበው ምስልም በአየር መንገዱ የማይታወቅ እንደሆነም ጠቅሷል።

አየር መንገዱ ከብሔር ማንነት ጋር በተያያዘ ሰራተኞችን አሰናብቷል በሚል የቀረበበት ውንጀላም መሰረተ ቢስ ስለመሆኑ ተገልጿል።

ይህም በሰው ሃብት አስተዳደር ማህደር ሊረጋገጥ የሚችል መሆኑን አመልክቷል።

ባለፉት 10 ዓመታት በሁሉም መስክ አራት እጥፍ እድገት ያስመዘገበው አየር መንገዱ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን ይዞ እንዲቀጥል አስችሎታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሰቃቂውን የዓለም አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ለመቆጣጠር ክትባቶችና ንፅህና መጠበቂያዎች በማሰራጨት አጋርነቱ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተዛማጅ ደንቦችን እና መስፈርቶችን በጥብቅ የሚያከብር ፣ በሁሉም የሥራ ክንውኖች ውስጥ ከማንኛውም የሲቪል አቪዬሽን ደንቦች የማይወጣ፣ በጦር መሣሪያ ማጓጓዝ ተግባር ውስጥ ተሰማርቶ የማያውቅ መሆኑን ለሁሉም ወገን እንደሚያረጋግጥ ተገልጿል።

ስለሆነም በሲኤንኤን የተሰራጨው ዘገባ ስህተት በመሆኑ እርማት እንደሚያስፈልገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም