ዩኒቨርሲቲው ከ160 በላይ ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርጓል

54

ጎባ፣ መስከረም 28/2014(ኢዜአ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በክረምት የዜግነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ160 በላይ ለሆኑ  አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች የአካል ድጋፍና የመኖሪያ ቤት እድሳት ማካሄዱን ገለጸ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ሽፋ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለይ በግብርና፣ በጤና፣ በነጻ የህግና በሌሎች ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የትኩረት መስኮች ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ለተለዩ 163 አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ያደረገው ክራንች፣ ዊልቼር፣ ጫማዎችና የምግብ ዱቄት የዚሁ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተለይ ዩኒቨርሲቲው በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሮቤ ከተማ ለሚኖሩ ስድስት አቅመ ደካሞች ያደረገው የመኖሪያ ቤት እድሳት በመልካምነት ከሚጠቀሱት ተግባራት መካከል ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሁለቱ የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ያከናወናቸው ተግባራት በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተገልጿል። 

ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያደርጋቸው የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

የሮቤ ከተማ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረጋሳ ጅማ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለአቅመ ደካማ፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተማሪዎች የእህል፣ የአካል ድጋፍ ቁሳቁስ በመስጠትና መኖሪያ ቤቶችን በማደስ ማገዙንም አስረድተዋል።

በሮቤ ከተማ የመኖሪያ ቤት የታደሰላቸው የጨፌ ዶንሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ኡስማን በበኩላቸው "ቤቴ አርጅቶ ሊወድቅ በማዘመሙ አንድ ቀን በልጆቼ ላይ ይወድቅብኛል የሚል ስጋት ውስጥ ነበርኩኝ” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ይሄንን ችግር በማየት እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸው "ከዚህ ስጋት ያላቀቀኝን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲን አመሰግነዋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያደረገልን የአካል ድጋፍ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ያሰብኩትን ለመፈጸም እንድችል ረድቶኛል ያሉት ደግሞ የአካል ድጋፍ(ክራንች) የተሰጣቸው አቶ መንግስቱ ከተማ ናቸው።


በ1999 ዓ.ም የመማር ማስተማሩን የጀመረው መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ24 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች የማስተማር አቅም መፍጠሩን የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም