የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ወስጥ መካተታቸው ሀገር የጋራ መሆኑን በተግባር ያረጋጋጠ ነው

86

አዲስ አበባ መሰከረም 27/2014 የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መካተታቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ባሻገር ሀገር የጋራ መሆኑን በተግባር ያረጋጋጠ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የቀረቡ የ22 የካቢኔ አባላትን ሹመት አጽድቋል።

በምክር ቤቱ ሹመታቸው ከጸደቀው የካቢኔ አባላት መካከል ደግሞ ሶስቱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው።

ኢዜአ የካቢኔ ሹመቱን በሚመለከት በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መካተታቸው የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ወይዘሮ ጥሩወርቅ ኃይሌ የካቢኔ አወቃቀሩ አካታች የፖለቲካ አመለካከትን ያንጸባረቀ ነው ይላሉ።

በአንድ የፖለቲካ አመለካከት የታጠረና አገር የአንድ ፓርቲ ብቻ ነች የሚለውን አስተሳሰብ የቀየረና ዘመናዊ ፖለቲካን የሚያላምድ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ሂደቱ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከማፋጠን አኳያ በጎ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

አቶ አደራዬ አየለ በበኩላቸው የምክር ቤቱ ስብሰባ ብዝሃ አተያይ የጎላበትና የሃሳብ ነጻነት የነገሰበት መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።

የካቢኔ ምልመላው ከፖለቲካ አመለካከት ይልቅ ለትምህርት ዝግጅትና ስራ ልምድ ቅድሚያ መስጠቱ ሹመቱን ፍትሃዊ እንዳደረገውም ነው ያነሱት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አወል አሊ፤ "6ኛው አገራዊ ምርጫ በምርጫው ወቅት ብቻ ሳይሆን በውጤቱም ስኬታማ መሆኑ በካቢኔ ሹመት ማየት ተችሏል" ብለዋል።

ይህም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ምክር ቤት ውስጥ ካገኙት ወንበር በተጨማሪ በመንግስት ካቢኔ ውስጥ መካተታቸው በአገሪቱ የዲሞክራሲ ባህል እየዳበረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር ጉዳይ ላይ መገፋፋት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያሉት ደግሞ አቶ ቦጋለ ቸርነት ናቸው።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣የመንግስት አካላት እንዲሁም ሁሉም ዜጋ የሚለፋው ለአንዲት ኢትዮጵያ መሆኑን አንሰተው፤ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልልም የታየው ጅማሮ ለአገር እድገት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ -የትምህርት ሚኒስትር፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ - የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የቀረበውን ሹመት ማጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም