ወደ ጣና ሃይቅ በየዓመቱ ስድስት ሚሊዮን ቶን አፈር እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ

210
ባህር ዳር ነሀሴ 11/2010 ወደ ጣና ሐይቅ በየዓመቱ ስድስት ሚሊዮን ቶን አፈር እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የተካሄደ ጥናት አመለከተ። ባለፉት ዓመታት ከሃይቁ የላይኛው ተፋሰስ ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሰራም በሳይንሳዊና ዘመናዊ እውቀት ባለመታገዙ ችግሩን ማስቆም እንዳልተቻለ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ማዕከል  ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ጌቴ ዘለቀ እንደገለጹት በየዓመቱ ስድስት ሚሊዮን ቶን የአፈር ደለል ወደ ጣና ሃይቅ እንደሚገባ በጥናታቸው አረጋግጠዋል። በጣና ሃይቅ ተፋሰስ ከላይኛው ክፍል ጀምሮ ባለፉት ዓመታት እየተሰራ ያለው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ሃይቁን ከጉዳት እንዳልታደገው ተናግረዋል። በዚህም የሃይቁ ገባር የሆኑት የርብ ፣ መገጪ፣ ግልገል አባይና ሌሎች ወንዞች በክረምት ወቅት የሚያመጡትን ደለል ማስቆም አለመቻሉን ተናግረዋል። ''በሃይቁ ዙሪያ እየተሰራ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በዘፈቀደ በመሆኑ በሃይቁ ላይ እንቦጭ ከተባለው መጤ አረም ያልተናነስ በደለል የመሞላት አደጋ ተጋርጦበታል'' ብለዋል። ''ከየአቅጣጫው በሚመጡ ገባር ወንዞች የሚመጣውን ደለል ለመቀነስና ሃይቁን ከጉዳት ለመታደግ በሃይቁ ዙሪያ የሚሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ስራዎች ሳይንሳዊ ዘዴ የታገዙ ሊሆን ይገባል'' ሲሉ አሳስበዋል። እንደ ዶክተር ጌቴ ገለጻ በዓለም ላይ ሃይቅ ሆኖ ዝናብ በዘነበ ቁጥር ቀለሙ የሚቀይር የለም፤ የጣና ሃይቅ ግን  ዘጠኝ ሜትር አማካኝ ጥልቀት እንዳለው ቢታመንም በደለል ከመሞላቱ የተነሳ ዝናብ በዘነበ ቁጥር የውሃው ከለር ወደ አፈርነት እንደሚቀየር ገልፀዋል፡፡ “ይህ ደግሞ ሃይቁ በከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑን ማሳያ በመሆኑ ስትራቴጂክ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ሊሰራለት ይገባል” ብለዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ እንዳሉት በሃይቁ ላይ እየደረሰ ያለው በደለል የመሞላት ችግር በዘላቂነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በሃይቁ ተፋሰስ ከላይኛው ክፍል ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ያሰገኘውን ውጤት፣ የነበሩ ክፍተቶችንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ጥናት በምሁራን ማስጠናቱን ገልጸዋል። የጥናቱ ውጤት እንዳረጋገጠውም በሃይቁ ላይ እየደረሰ ያለው በደለል የመሞላት አደጋ ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ በቀጣይ የሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በባለሙያ ታግዞ እንዲከናወን የሚያስችል ግኝት ነው። በግኝቱ መሰረትም በተፈሳሰሱ ላይ የሚሰራው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በዘርፉ ያሉ ምሁራንን ባሳታፈ መልኩ በማከናወን ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ በሃይቁ ላይ የተጋረጠው አደጋ ለመከላከልም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባለድርሻ ኣካላትን ያሳተፈ ውጤታማ ተግባር ለማካሄድ መግባባት መደረሱ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም