አበረታች መድሐኒት የኬንያ አትሌቲክስ ስጋት ሆኗል

152
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010  ከአበረታች መድሐኒት ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ስሟ የሚነሳው ኬንያ ከሰሞኑ ባለፈው ዓመት ለንደን ላይ በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች 800 ሜትር ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘው ቤት ኪፕዬጎን አገሪቱን ከሰሞኑ መነጋገሪያ እንድትሆን አድርጓታል። አትሌት ቤት ኪፕዬጎን በአበረታች መድሐኒት ያደረገውን ምርምራ ናሙና ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአትሌቲክስ የስነምግባር የስራ ክፍል ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከውድድር እንዲታገድ ውሳኔ ተላልፎበታል። አትሌቱ የናሙናውን ውጤት እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ መስጠት የነበረበት ቢሆንም ናሙናውን ሊሰጥ አልቻለም። ከሳምንታት በፊት የማራቶን ሯጭ ሳሙኤል ካሌሊ የአበረታች መድሐኒት ወስዶ በመገኘቱና የማራቶን ሯጯ ሉሲ ካቡ በአበረታች መድሐኒት ምርመራ ወቅት አበረታች መድሐኒት ወስዳ በመገኘቷ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እገዳ እንደጣለባቸው የሚታወስ ነው። ሌላኛው ኬንያዊ የ400 ሜትር ተወዳዳሪ ቦኒፌስ ምዌሬሳ በተደረገለት ምርመራ አበረታች መድሐኒት ወስዶ በመገኘቱ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል። ኬንያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከሚያስጠሩት ታዋቂ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው የ 1 ሺህ 500 ሜትር ሯጩ አስቤል ኪፕሮፕ ከወራት በፊት አበረታች መድሐኒት እንዳልወሰደ ቢናገርም በተደረገበት ምርምራ መድሐኒት መጠቀሙ ስለተረጋገጠ እገዳ እንደጣለበት ይታወቃል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የማራቶን ሯጮቹ ሬታ ጂፕቶና ጄሚና ሱምጎንግ በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እገዳ እንደጣለባቸው የዓለም መገናኛ ብዙሃን በትውስታ እያነሱት ይገኛሉ። ሰሞኑን በኬንያ አትሌቶች ላይ ከአበረታች መድሐኒት ጋር በተያየዘ እየወጡ ያሉ መረጃዎች በአገሪቷ ያለውን የአትሌቲክስ ማህበረሰብ ማስደንገጡና ስጋት መፍጠሩን የአገሪቷ ጋዜጣ ዴይሊ ኔሽን በድረ ገጹ አፍሯል። እየተነሱ ያሉት ጉዳዮች በመካከለኛና ረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝና ያላትን ኬንያ ስጋት ውስጥ የሚከትና በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበረሰብ ትኩረቱን ወደሷ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአትሌቲክስና በሌሎች ስፖርቶች በአበረታች መድሐኒት የዓለም መነጋገሪያ የሆነችው ሩሲያ በመቀጠል ኬንያ በአትሌቲክሱ የአበረታች መድሐኒት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆናለች። የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም በተደጋጋሚ የሚሰሙ ዜናዎች ግን ፌዴሬሽኑንም ስጋት ውስጥ ሳይከተው አይቀርም። በሌላ በኩል በአትሌቲክሱ በአበረታች መድሐኒት ጉዳይ ስማቸው ሲነሱ ከነበሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች የሚታወቅ ሲሆን አንዳንድ አትሌቶችም አበረታች መድሐኒት በመወሰድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እገዳ ተጥሎባቸዋል። ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ''ኢትዮጵያ በአበረታች መድሐኒት ያለውን ችግር ለመፍታት ሰፊ ምርምራ ታድርግ አለበለዚያ ቅጣት ይተላለፍባታል'' የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥቶ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ከቀረበለት ሀሳብ በመነሳት በአትሌቲክስ ስፖርት የሚነሳውን ከአበረታች መድሐኒት ጋር በተያያዘ ህጋዊ ርምጃ የመወሰድና የማስተማር ስራ በመስራት ላይ ይገኛል። ጽህፈት ቤቱ በ2010 ዓ.ም አትሌት ብርቱካን አደባ፣ አትሌት ኢዮብ ዓለሙ፣ አትሌት ሐይሌ ቶሎሳና አትሌት አሊ አብዶሽ አበረታች መድሃኒት ተጠቅመው በመገኘታቸው ለአራት ዓመታት በየትኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፉ ቅጣት ማስተላለፉ ይታወሳል። በቀጣይም አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ-አብረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጹ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ከወሰዳቸው ህጋዊ እርምጃዎች በተጨማሪ ከስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የመስጠት ተግባርም እያከናወነ ይገኛል። ጽህፈት ቤቱ የሚያከናውነውን ተግባር የዓለም አቀፉ የጸረ- አበረታች መድሐኒት ድርጅት (ዋዳ) የስራ ሃላፊዎች አድናቆት የሰጡት ሲሆን የተወሰዱ እርምጃዎች አበረታችና ሊቀጥሉ የሚገባቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራርም አበረታች መድሐኒት በሚወስዱ አትሌቶች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድና ጉዳዩ የአገርን ስም የሚያጠፋ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም