የእቀባ እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳገዛቸው የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ

80
ሶዶ ሰኔ 11/2010 የእቀባ እርሻን ተግባራ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዛቸው መሆኑን የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የግብርናና እንስሳት ሃብት ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች በዞኑ የእቀባ እርሻ ተግባራዊ የተደረገባቸውን ሁለት ወረዳዎች ጎብኝቷል፡፡ ''የጠረዼዛ ልማት ማህበር'' ተብሎ በሚጠራ ሃገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት አስተባባሪነት የተጀመረው የእቀባ እርሻ መሬትን በአካባቢው በሚገኝ ቅጠላ ቅጠል ሸፍኖ ሳያርሱ በማቆየት ለምነቱ እንዲመለስ የማድረግና መላልሶ ማረስ የማይፈልገው የአስተራረስ ዘዴ ነው፡፡ በዳሞት ወይዴ ወረዳ ጋልቻ ሳኬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈለቀ ዶራ የእቀባ እርሻን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ የእቀባ እርሻ መላልሶ ማረስና ድካም አይጠይቅም ያሉት አርሶ አደሩ መሬቱ በቅጠላ ቅጠል ተሸፍኖ ስለሚከርም ከጸሃይ፣ ነፋስና ጎርፍ እንደሚጠበቅና ለምነቱ እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ለምነቱየ ጨምሮ የተሻለ ምርት እያስገኘላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመሬቱ ለምነት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀው ባለፈው ዓመት በበቆሎ ባደረጉት ሙከራ ከአንድ ጥማድ እስከ 30 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ጎደሬና በሌሎችም የሰብል ዓይነቶች እያሰፉ በመምጣታቸው ከእለት ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ምርት እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ የእቀባ እርሻ ከጀመሩ ከሶስት ዓመት ወዲህ መሬታቸውን በቅጠላ ቅጠል በመሸፈንና ሳይታረስ በማቆየት ለምነቱ እንዲጠበቅ ማድረጋቸውን የገለፁት ደግሞ በሁምቦ ወረዳ አባላ ቆልሾቦ ቀበሌ አርሶ አደር ፈለቀች ተካ ናቸው፡፡ ተሸፍኖ የቆየውን መሬት ሳያርሱ በቁፋሮ ብቻ በመዝራት በመጀመሪያ ዓመት ከአንድ ጥማድ ማሳ ካለሙት በቆሎ  28 ኩንታል፤ ጎዴረ ደግሞ ከ80 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ማሳቸውን ደጋግሞ እንዲታረስ ለጉልበት ሰራተኞች እንዲሁም የተለያዩ ግብአቶች ለመግዛት የሚወጡትን ወጪ እንደቀነሰላቸውም ገልፀዋል፡፡ የጠረዼዛ ልማት ማህበር ሥራ አስከያጅ አቶ በረከት ጣሰው በበኩላቸው  ዞኑ ዝናብ አጠርና ከፍተኛ ህዝብ የሚኖርበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የምግብ እጥረትና ተረጂ ቁጥር ለመቀነስ የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አፈርን መሸፈን፤ በጥቂቱ ማረስና ሰብልን ማፈራረቅ የእቀባ እርሻ መርሆዎች ናቸው ያሉት አቶ በረከት በማሳ ዝግጅት ወቅት ጉልበት ለመቀነስ፣ በአንድ ማሳ የተለያየ ሰብል ለማምረትና የሰብል በሽታ ለመከላከል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጠዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም 40 ፈቃደኛ አርሶ አደሮች በማሰልጠን ለሙከራ የተጀመረው የእቀባ እርሻ ዛሬ ላይ ከ11 ሺህ በላይ መድረሱንና በአጠቃላይ በዞን ደረጃ ከ500 ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑንም ተናግረዋል፡፡ በምርታማነት ደረጃ ከመደበኛ እርሻ እንደየሰብሉ ሁኔታ እስከ 70 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸው አሁን ላይ የህዝቡ ጥያቄ በመብዛቱ መንግስት ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክፋለ ታውለ በበኩላቸው የህዝብ ጥግግት ከፍተኛ በሆነበት፣ ዝናብ አጠርና በተለያዩ ምክንያት የአፈር ለምነት እየቀነሰ በመጣበት አካባቢ የእቀባ እርሻን ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር በመሬት ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ መሰንበት ተስፋዬ በበኩላቸው የእቀባ እርሻ በሰፊው ቢተገበር የመሬት ለምነትን በመመለስ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ እንዲሁም የአፈር ለምነትና እርጥበት በመጠበቅ የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በጥቂት ማሳ ሳያቋርጡ ምርትን ለማግኘት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የእቀባ እርሻ በደቡብ፣ በጋምቤላና በአማራ ክልሎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን የገለፁት አቶ መሰንበት በቀጣይ በመንግስት በፖሊሲ ማዕቀፍ ታግዞ አሰራሩን ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም