አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወርና በመጠቀም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ዋሉ

71

ጭሮ፤ መስከረም 25/2014(ኢዜአ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ፖሊስ አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀሙና ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በህብረተሰብ ጥቆማ ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የጭሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚካኤል ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግለሰቦቹ አደንዛዥ ዕፁን ከሚያመርት ሰው  በመረከብ እየተጠቀሙ ለሌሎች በማከፋፈልና ከሸቀጦች ጋር ሲሸጡ ተደርሶባቸዋል።

ይህም ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ቤት ሲፈተሽ 20 ኪሎ የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ እንደተገኘባቸው አስረድተዋል፡፡

በግቢው ውስጥ ሀሺሽ ዘርቶ እያስፋፋ ያለ ግለሰብ ለጊዜው ሸሽቶ ቢያመልጥም በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ኢንስፔክተር ሚካኤል አስታውቀዋል፡፡

አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ሰዎች  በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ እንዲሁም የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር ስለሚያደርጉ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በመጠቆም ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀምና ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር የዋለው አንዱ ግለሰብ በሰጠው አስተያየት፤  ቀደም ሲል በድለላ ስራ ይተዳደር እንደነበርና ከጓደኞቹ ጋር በአጋጣሚ እንደመዝናኛ እንደጀመረው ይናገራል፡፡

ዕፁን  በሚወስድበት  ወቅት እራሱን  መቆጣጠር እየተሳነው ከቤተሰብና ህብረተሰቡ ጋር በሰላም መኖር መቸገሩን ገልጿል፡፡

አደንዛዥ ዕፁን የሚያገኘው  በምዕራብ ሐረርጌ መጣቀሻ ጢቆ ከምትባል አካባቢ የሚኖር ግለሰብ ከሌሎች የሰብል ምርቶች ጋር ቀላቅሎ እያመረተ እንደሚያመጣለት አስረድቷል፡፡

ሌላው ተጠርጣሪ በበኩሏ፤ ማንነቷን የማታውቃት ሴት ከአዲስ አበባ እያመጣች እንዴት እንደሚሰራ ስልጠና ከሰጠቻት በኋላ ወደ ስራው እንዳስገባቻት ትናገራለች፡፡ 

በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ከልጆቿና ሌሎች ሰዎች ጋር የነበራትን መልካም ግንኙነት በመበላሸቱ መረበሿንና በዚህም መፀፀቷን ገልጻለች።

ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በቀጣይ ከዚህ ሱስ ተላቀው ከቤተሰባቸውና ማህበረሰቡ ጋር በሰላም መኖር እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም