12ኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር በእንግሊዝ በርሚንግሀም ነገ ይካሄዳል

68
አዲስ አበባ ነሃሴ 11/2010 የ2018 (እአአ) 12ኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር እንግሊዝ በርሚንግሀም ከተማ ነገ ይካሄዳል። ያለፉት 11 ዙሮች የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በሰሜን አሜሪካና አፍሪካ አህጉሮች በሚገኙ ከተሞች መካሄዳቸው ይታወሳል። ነገ ከቀኑ ሰባት ሰአት ጀምሮ በአሌክሳንዳር ስታዲየም በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ይሳተፋሉ። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት አክሱማዊት አምባዬ፣ አትሌት አልማዝ ሳሙኤልና አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ይወዳደራሉ። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ እስካሁን በዳይመንድ ሊጉ በርቀቱ ባደረገቻቸው ውድድሮች 23 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ለታላቋ ብሪታኒያ የምትወዳዳደረው ላውራ ሙር በ25 ነጥብ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች። አትሌት ጉዳፍ በነገው ውድድር ካሸነፈች በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያ ደረጃን የምታገኝ ይሆናል። በ3 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ትሳተፋለች። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች በርቀቱ እስከአሁን በዳይመንድ ሊጉ በተካሄዱ ውድድሮች ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አትሌት ጫላ በዩ ይሳተፋል። ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪገን 21 ነጥብ ሰብስቦ የመሪነቱን ቦታ ይዟል። አሌክሳንዳር ስታዲየም በ17 ርቀቶች የሚካሄዱ ውድድሮችን ያስተናግዳል። በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ለተሰንበት ግደይ እስካሁን 17 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ቀጣይ ውድድሮችን ማሸነፍ ከቻለች አሸናፊ የመሆን እድሏን ከፍ ታደርጋለች። አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ11 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ15 ነጥብ እንዲሁም አትሌት ሙክታር እድሪስና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በተመሳሳይ 14 ነጥብ ይዘው በተመሳሳይ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነው ብርሃኑ ባለው በርቀቱ እስካሁን በተደረጉ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች 25 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን ይዟል። በ14 ከተሞች የሚካሄደው የዘንድሮው ዓመት የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 24 ቀን 2010 በስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ እና ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራሰልስ በሚካሄዱ ውድድሮች ፍጻሜውን ያገኛል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በአጠቃላይ ድምር ውጤት ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት አዘጋጅቷል። በየርቀቱ የሚያሸንፍ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የ50 ሺህ ዶላርና የዳይመንድ ሽልማት ይበረከትለታል። በተጨማሪም የዓመቱ ምርጥ አትሌት ስያሜን የሚያገኝ ሲሆን በቀጣይ ዓመት በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ በሚካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሳተፉን ያረጋግጣል። የዳይመንድ ሊግ ውድድር እአአ ከ1998 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውን ጎልደን ሊግ ከ12 ዓመታት በኋላ በመተካት እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም