እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በሊግ አደረጀጀትና የተጫዋቾች ዝውውር ደንብ ዙሪያ ከኘሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ውይይት አካሄደ

64
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሊግ አደረጀጀትና የተጫዋቾች ዝውውር ደንብ ዙሪያ ከኘሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል የጋራ ውይይት አካሄደ፡፡ የሊግ አደረጀጀትን አስመልክቶ በተደረገ ውይይትም ሊጉን ለማደራጀት ሰፊ ጊዜ ጉልበትና ገንዘብ ስለሚጠይቅ ይህንንም ለማስፈፀም የሚረዳ ጥናት እየተካሄደ ስለሆነ የጥናቱ ውጤት ታውቆ ከክለቦች ጋር የጋራ ውይይት ተደርጎ እንደሚወስን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኘሪሚየር ሊግ ውድድርን ለማስጀመር የ2010 ዓ.ም የሊግ አፈፃፀም ሁኔታና አመራር ሂደትን በተመለከተ በአጭር ጊዜ አጠቃላይ ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ግምገማ እንዲደረግበትና የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግር ከመንግሥት ጋር በመሆን በጥልቀት እንዲታይም ተግባብተዋል። የ2011 ዓ.ም ውድድርን ለመምራት ፌዴሬሽኑ ባቀረበው አማራጭ ሃሣቦች መሠረት ከክለቦች 3 እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ 3 ሰው የተውጣጡና በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተመደቡት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ሰብሳቢነት ሰባት አባላት ሆነው የሊጉን ውድድር እንዲመሩ ለዚህም ክለቦች እጩ ተጠቋሚዎችን በሚቀጥለው ጊዜ እንዲያቀርቡ መስማማታቸው ታውቋል። የተጫዋቾች ዝውውር ደንብና መመሪያን በተመለከተም የኘሮፌሽናል ተጨዋቾች ዝውውር በዝውውር ደንብ ውስጥ እንዲካተት ሆኖ ይህም ሲባል ከፊፋ የዝውውር ደንብ ጋር የተገናዘበ እንዲሆን ተነጋግረዋል። በአንድ ክለብ ውስጥ ሊኖሩ ስለሚገባቸው የውጭ ሀገር ተጨዋቾች ብዛትም ሰፊ ውይይት ተካሂዶ በአብዛኛው 3 ይሁን በሚል ሃሣብ የቀረበ ሲሆን ይህም በጥናት በሚቀርበው መነሻ ሀሳብ ላይ ክለቦች ተወያይተው በሚሰጠው ውሣኔ መሠረት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ተግባብተዋል። የተጫዋቾች የደመዋዝ ጣሪያን በተመለከተም ወደፊት የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንዲታይ የሚሉና ሌሎችም ነጥቦች በስብሰባው ላይ ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ይህም ወደፊት እንዲታይ መወሰኑን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በአጠቃላይ የነበረው ውይይት እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እያስጠና ላለው ሪፎርም ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት ሆኖ መጠናቀቁም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም