የለውጥ እንቅስቃሴው ህዝቡን በማስተባበር እንደሚያጠናክሩ በምስራቅ ወለጋ የኦህዴድ አባላት ገለጹ

63
ነቀምቴ ነሀሴ 10/2010 በሀገሪቱ የመጣውን የለውጥ እንቅስቃሴ ህዝቡን በማስተባበር ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በምስራቅ ወለጋ ዞን የኦህዴድ አባላት ገለጹ። አመራሩና አባላቱ በአዲሱ የድርጅቱ አርማና በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ  ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ያካሄዱትን ኮንፍረንስ ሲያጠናቅቁ እንዳሉት የህግ የበላይነትን በመጠበቅ የተገኘው ለውጥ  እንዳይቀለበስ ጠንክረው ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከኮንፍረንሱ ተሳታፊ አባላት መካከል አቶ አሰፋ ገርቢ በሰጡት አስተያየት ከአሁን በፊት የድርጅቱ አባላት ከህዝብ አገልጋይነት ይልቅ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲሯሯጡ መታየቱን ተናግረዋል። ተሃድሶ ያፈራቸው ጠንካራ አመራር ከመጣ ወዲህ ችግሩ እየተቃለለ መምጣታቸውን አመልክተው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተገኘው ለውጥ እንዳይቀለበስ ህዝቡን በማስተባበር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ለአከባቢውና ለሃገሪቱ ፈተና እየሆነ የመጣውን የሰላምና የጸጥታ ችግር ለማስወገድ ሁሉም ዜጋ ሊተባበር እንደሚገባም አሳስበዋል። ሌላው የድርጅቱ አባል አቶ ተስፋዬ አስጨናቂ በበኩላቸው አሁን የተገኘው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ከሁሉም በላይ የአባላቱ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል። አቶ ተስፋዬ እንዳሉተ ባለፉት 27 ዓመታት የነበሩት ችግሮችን በመፍታት ለሀገር ልማትና እድገት የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል። የተገኘው ለውጥ ከአፍሪካ አልፎ ዓለምን ያስደመመና በቀጣይም ከህዝቡ ጎን በመቆም ለማጠናከር እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ አቶ ሁሉማ በቀለ ናቸው። የህግ የበላይነት በማስከበር በሀገሪቱ የመጣውን የለውጥ እንቅስቃሴ የህዝቡን የተቀናጀ ተሳትፎ በማስተባበር  ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አባላቱ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል። የዞኑ ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሶ ተመስገን በውይይቱ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግገር "  ከተሃድሶ በፊት አንድነታችን እንዳይጠናክር የሚያደርጉ አካላት  ስለነበሩ በሁሉም መስክ የሚፈለገው ውጤት ሊገኝ አልቻለም" ነበር ብለዋል፡፡ አሁን የተገኘውን ለውጥ ለሕዝብ ተጠቃሚነትና ለሀገር እድገት በማዋል የህግ የበላይነትና ዘላቂ ሰላምን እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በኮንፍረንሱ አዲስ በቀረበው የድርጅቱ ዓርማ  ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በቀጣይ እስከ ታችኛው መዋቅር ምክክር እንዲደረግበትም ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም