ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ለማድረግ ለተፈናቃዮች መጠለያ እየተገነባ ነው

81

ደሴ ፤ መስከረም 23/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች ለተጠለሉ ወገኖች የሚያገለግሉ መጠለያዎች እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚገነባ  የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የአደጋ ምላሽና ክትትል ቡድን መሪና በደሴና አካባቢዋ የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ ታዬ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈፀመው ወረራ ተፈናቅለው ደሴና ኮምቦልቻ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ350 ሺህ በላይ ነው።

ከዚህ ውስጥ 14 ሺህ የሚደርሱት ተፈናቃዮች በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ 28 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልፀዋል።

አሁን ላይ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር እንቅስቃሴ በመጀመሩ ትምህርት ቤቶች ተፈናቃይ አገልግሎት ከመስጠት  ወጥተው መደበኛ ስራቸውን እንዲጀምሩ ለማድረግ ኮሚሽኑ ኮሚቴ አዋቅሮ በቅንጅት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ በደሴ ከተማ ሁለት፤ በኮምቦልቻ ከተማ ደግሞ አንድ በድምሩ ሶሰት መጠለያ ካምፖችን ለመገንባት ከሦስተኛ ወገን ነፃ የሆነ የግንባታ ቦታ ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ርክክብ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የመጠለያ ካምፖቹ ግንባታም እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንደሚቻል አስረድተዋል።

የግንባታ መዘግየት ቢገጥምና የትምህርት መጀመሪያው ወቅት ቢደርስ ተፈናቃዮች ወጫቸው ተሸፍኖ ለጊዜው ቤት እንዲከራዩ በማድረግ በመማር ማስተማሩ ስራው ላይ ጫና እንዳይፈጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተፈናቃይ ልጆችም በአሉበት አካባቢ ተመዝገበው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከመደረግ ባለፈ እንደ አስፈላጊነቱ በካምፖች አካባቢ ጊዜያዊ ትምህርት ቤት ሊሰራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ሁሴን በበኩላቸው ከ20 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከቀያቸው ተፈናቅለው በኮምቦልቻ ከተማ መጠለላቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ5 ሺህ የሚበልጡት በ10 ትምህርት ቤት የተጠለሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይሄም በትምህርት ቤቶቹ መደበኛ ትምህርት ለማስጀመር ችግር መፍጠሩን አመልክተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተማው በሚገኙ 29 ትምህርት ቤቶች ውስጥ  ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን ከ80 በመቶ በላይ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ለተፈናቃዮች መጠለያው  ተገንብቶ ትምህርት ቤቱን ከለቀቁ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር እንደሚችሉ የገለጹት ደግሞ የኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አበበ ብርሃኑ ናቸው፡፡

በትምህርት ቤቱ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል ከወልድያ ከተማ የመጡት አቶ ሁሴን ሰይድ  ''የመማር ማስተማር ስራው እንዳይስተጓጎል መንግስት መጠለያ ካምፕ ፈጥኖ በመገንባት ሊያዘዋውረን ይገባል'' ብለዋል።

የእነርሱም ልጆች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ አካባቢያቸው ሰላም ሆኖ ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ  ትምህርት የሚያገኙበት እድል እንዲመቻችም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም