ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልዩነቶችን አጥብበው በጋራ ቢሰሩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለፀ

66
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በጋራ መስራት ለአገር አቀፍ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር እንደሚያግዝ ተገለፀ። በአገር አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ላይ ያተኮረ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዛሬ ተካሄዷል። በቅርቡ ከውጭ የገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከ50 በላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል። የፓርቲዎቹ ተወካዮች በሰጡዋቸው አስተያየቶች “የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ ተግባብተው በጋራ መስራት ሳይችሉ አገር አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ሊፈጥሩ አይችሉም” ተብሏል። የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሐላፊ አቶ አበበ አካሉ “እንዲህ 70 እና 80 የፖለቲካ ፓርቲ ሆነን ሳንቀራረብ አገራዊና ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና ህዝብን ማስታረቅ አንችልም” ብለዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ እየተናቆርን "ህዝብን በድለናል ይቅርታ መጠየቅ አለብን”  ሲሉም ተናግረዋል። የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፕሬዚዳንት አቶ ትግስቱ አወሉ በበኩላቸው “እኛ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እርስ በርሳችን ዕርቅ ያስፈልገናል፤ እኛ ራሳችን ሳንግባባ አገራዊ መግባባት መፍጠር አንችልም" ሲሉ ተደምጠዋል። “እኛ ራሳችን እርስ በርስ መፈራረጅ እናቁም” ያሉት ደግሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው።  እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ "በመጀመሪያ በመካከላችን መግባባትና ዕርቅ በመፍጠር ለሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ምሳሌ መሆን አለብን" ብለዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄም  የፖለቲካ ፓርቲዎች “በአሁኑ  ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን አንድነትን የሚፈታተን ግጭት፣ የሰው ህይወት መጥፋትና የዜጎች መፈናቀል ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል። ይሄን አገራዊ ግዴታ ለመወጣት ደግሞ "ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተቻችሎ መሄድን ይጠይቃል፤ ይሄን ማድረግም ይኖርብናል" ነው ያሉት። የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አንዱአለም ጥላሁን በበኩላቸው በአገሪቱ የህግ የበላይነት እየተጣሰ ዜጎች ለህልፈትና መፈናቀል እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል። የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ያሉት አቶ አንዱአለም፤ መንግስት ያለውን አቅም ተጠቅሞ በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። የውይይት መድረኩን የመሩት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም እንደገለፁት በየአካባቢው እየታየ ባለው የህግ ጥሰት፣ የህዝብ መፈናቀልና የሰው ህይወት ማጣትን ለማስቆም የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር በተወለዱባቸው አካባቢዎች እየሄዱ ሊሰሩ ይገባል። ይሄን ለማድረግ ግን እርስ በርስ መግባባትና መቀራረብ እንዲሁም ከአገር ሽማግሌዎችና ከኃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን የተግባር ሥራ ማከናወን አለባቸው ነው ያሉት። በውይይቱ የተገኙት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መቀራረብና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብለው በጋራ መመካከርና መስራት ከጀመሩ ብዙ አገራዊ ችግሮች ይቀረፋሉ ብለዋል። ይሄም  በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ  ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር እየታዩ ያሉትን ችግሮች በጋራ እየቀረፉ ለመሄድ ጥሩ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል። የውይይቱ አዘጋጅ ከሚቴ አባል ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው በውይይቱ የተነሱ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በአገራዊ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ላይ ያተኮረ መድረክ በቅርቡ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች በመሄድ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር፣ ሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ሥራዎችን ለማከናወን በውይይት የተነሳው ሐሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር እንሰራለን ብለዋል። እነዚህን አጀንዳዎች ተግባራዊ ለማድረግም ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ኮሚቴዎች መስርተን ወደ ተግባር ለመግባት እንሰራለን ብለዋል። በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጎን ለጎን እየታየ ያለው የግጭት፣ ዜጎች መፈናቀልና የሰው ህይወት መጥፋት ለማስቆምና የህግ የበላይነት ለማስከበር መንግስት ኃላፊነቱ ሊወጣ እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም