አንጋፋው የቀድሞ የኢዜአ ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ አረፈ

88

መስከረም 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንጋፋው የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ጋዜጠኛ ጋሻው በኢዜአ ውስጥ በተለያየ ደረጃዎች ለ20 ዓመታት በጋዜጠኝነት አገልግሏል።

ከአባቱ አቶ ጫኔ ብዙነህ እና እናቱ ወይዘሮ የሽመቤት ታዬ በኦሮሚያ ክልል በቀድሞ ኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ በ1958 ዓ.ም የተወለደው ጋዜጠኛ ጋሻው የቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ነበር።

ጋዜጠኛ ጋሻው ከ30 ዓመታት በላይ በኢዜአ፣ በቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤትና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋዜጠኝነት፣ በአርታኢነትና ሌሎች ተያያዥ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥራዎች አገልግሏል።

በመቱና ጋምቤላ ከተሞች በሚገኙ የኢዜአ ቅርንጫፍ በወኪልነት ከዚያም በአዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት ከዜና ሪፖተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነተ ያገለገለ ድንቅ ባለሙያ ነበር።

ጋዜጠኛ ጋሻው በዜና አፃፃፉ የተዋጣለት የነበረ ከመሆኑም በላይ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ሳቢ መጣጥፎቹም በእጅጉ የሚደነቅ እንደነበር በተለይ የኢዜአ የሥራ ባልደረቦቹ ይገልፃሉ።

ከሁሉም ጋር በእጅጉ የሚግባባ እና ጨዋታ አዋቂም ነበር ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ።

ጋዜጠኛ ጋሻው ባጋጠመው ድንገተኛ ህመም በትናንትናው እለት አርፏል።

ጋዜጠኛ ጋሻው ባለትዳር ነበር።

የጋሻው ጫኔ የቀብር ሥነ-ስርዓትም ነገ መስከረም 24 ቀን ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ብሄረ ፅጌ ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን ይፈፀማል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋሻው ጫኔ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም