የሕዝቡን ጥያቄን በሚመልሱ ተግባራት ላይ ቅድሚያ ይሰጣል…አዲስ የተሾሙ የካቢኔ አባላት

105
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ፍላጎትና ጥያቄ ለመመለስ ለሚያስችሉ ተግባራት ቅድሚያ እንደሚያከናውኑ አዲስ የተሾሙ የካቢኔ አባላት ገለጹ። የካቢኔ አባላቶቹ  በሚያከናውኑት ተግባር ላይ  ከኢዜአ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ ከካቢኔ አባላቱ መካከል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች በየደረጃው የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ "የተጀመረውን ለውጥ ማፋጠን ይገባል"። ከዚህ ውስጥም በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ያለውን የሥራ ፍጎትና አቅርቦት በማጣጣም በሴቶችና በወጣቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ይዘረጋል ብለዋል። እስከ አሁን በከተማዋ የተከናወኑ ተግባራትን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የመዲናዋ ነዋሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ በበኩላቸው የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት አመራሩ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የገቢ ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው በአስተዳደሩ የሚካሄዱ የለውጥ ሥራዎችን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡  ከተማዋ በሁሉም መስክ ያላትን ሐብት በአግባቡ መጠቀም እንድትችልም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ ካቢኔው ስትራቴጂ ቀይሶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ እንዳሉት አስተዳደሩ የአመራር ለውጥ በማድረጉ ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አፋጣኝ ለውጥ ይጠበቃል ብለዋል። ህብረተሰቡ የሚያቀርበውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በመፍታት ረገድ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግም ወይዘሮ አልማዝ ተናግረዋል። የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው በመዲናዋ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እያንዳንዱ አካል የራሱን የቤት ስራ መስራት አለበት ብለዋል። የመዲናዋን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ የሕብረተሰቡን የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር ልምድ ለማጎልበትም ቢሮው እንደሚሰራም አስረድተዋል።  አዲሱ ካቢኔ በመዲናዋ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበውን ሪፎርም በብቃት እንደሚወጣም ታምኖበታል ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ  ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም