28 ነጥብ 6 ሚሊዮን የእርሻ ማሳዎችን በዘመናዊ የመሬት ካርታ ለማካተት እየተሰራ ነው

89
ባህርዳር ግንቦት 8/2010 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጨረሻ 28 ነጥብ 6 ሚሊዮን የእርሻ ማሳዎችን " ኦርቶ ፎቶ " በተሰኘ ዘመናዊ የመሬት ካርታ ለማካተት እየተሰራ መሆኑን የግብርና እና የእንስሳት ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ " መረጃን መሰረት ያደረገ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት " በሚል መሪ ሐሳብ  ከክልልና ከፌዴራል ከተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች ጋር  ዓመታዊ የመሬት ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው። በሚኒስቴሩ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ ገብረ መስቀል እንደገለጹት የመጀመሪያ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለመሬት አጠቃቀም የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የገጠር መሬት የመጀመሪያ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ የወል መሬቶች፣ የሴቶች፣ የህጻናትንና የአቅመ ደካማ መሬቶች ጉልበት ባላቸው እንዲመዘበር ሲያደርግ ቆይቷል። መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ " ኦርቶ ፎቶ " የተሰኘ ዘመናዊ የመሬት ይዞታ ካርታ ለመጠቀም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አስከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመት መጨረሻ 28 ነጥብ 6 ሚሊዮን የእርሻ ማሳዎችን " ኦርቶ ፎቶ " በተባለ ዘመናዊ የመሬት ካርታ ለማስነሳት ታቅዶ አየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁኑ 17 ሚሊዮን ማሳ ካርታ መነሳቱን ገለጸዋል። በእዚህም ስምንት ሚሊዮን አርሶ አደሮችም የካርታው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ያስረዱት። "ካርታው የመሬት ባለቤቶች ያላቸውን የመሬት መጠንና አዋሳኝ ድንበሮችን ግልጽ አድርጎ የሚያሳይና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት የሚያስችል ነው" ብለዋል። ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መተግበር የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት ሚኒስትር መሰሪያ ቤቱ  ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አቶ ትግስቱ ገለጻ በአገሪቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ የገጠር የእርሻ መሬቶች ይገኛሉ ። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም ዲን ዶክተር አቻምየለህ ጋሻው እንደገለጹት የመሬት አጠቃቀም የመረጃ አያያዝ ችግርና  ዘርፉን የሚመሩት አካላት የእውቀት ክፍተት ለገጠር መሬት ፍታዊ ተጠቃሚነት መጓደል ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዶክተር አቻምየለህ ገለጻ፣ የመሬት  አጠቃቀም ችግርን ለመቅረፍ ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ስርአትና ቴክኖሎጂውን በአግባቡ የሚተገብር የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲው የመሬት አጠቃቀም ስርአትን ለማዘመን በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ የሴክተር መስሪያ ቤቶችን አቅም የመገንባት ሥራ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም  ቢሮ ኃላፊ አቶ  አዳነ መሀሪ በበኩላቸው እንደገለጹት በክልሉ ውስጥ ያሉ ሁሉም የገጠር እርሻ መሬቶች  በ" ኦርቶ ፎቶ" ዘመናዊ  የመሬት ካርታ ተነስተዋል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ በላው ዓመታዊ የመሬት ኮንፈረንስ በሃሪቱ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና መሰል ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ሲሆን በመድረኩም የዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ምሁራን፣ የክልልና የፌደራል አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳተፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም