የተለያዩ የውጭ አገር ገንዘቦች በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

75
አዲስ አበባ ነሃሴ 10/2010 የተለያዩ የውጭ አገር ገንዘቦች በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ። ከ92 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና ሌሎችም የተለያዩ የውጭ አገር ገንዘቦች በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ነው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር የዋሉት። የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት ከነሐሴ 1 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በተደረገ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ብርን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚህም 92 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር፣ 13 ሺህ ዩሮ፣ 17 ሺህ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ድርሃም እና 54 ሺህ 600 የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት። ገንዘቦቹ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ብቻ በህገ-ወጥ መልኩ ከአገር ሊወጡ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሐምሌ ወር ብቻ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙን መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም