ጅማ ዩኒቨርሲቲና የአሜሪካው ቴክሳስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

76

ጅማ መስከረም 21/2021 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከቴክሳስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በምህንድስና ትምህርት የልህቀት ፈር ቀዳጅ የተሰኘ ፕሮጀክት አብሮ ለመስራት የኦን ላይን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኩል የፈረሙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ዋቅጅራ ናቸው።

ከቴክሳስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የተቋሙ ከፍተኛ ዳይሬክተር ሚስተር ኩይ ሩሙ የምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ኤሚ ኩክን በመወከል ሰምምነቱን ፈርመዋል።

የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ዋቅጅራ አንደገለጹት ፕሮጀክቱ አላማው የምህንድስና ትምህርትን የአለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ነው።

በምህንድስና የትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሚሰጡ ስልጠናዎች የቴክኒክ የስልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ለአምስት አመት የሚቆይ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል። 

የምህንድስናውን ትምህርት በማላቅ ሰልጣኞች ደረጃውን የጠበቀ እውቀት ማግኘት እንዲችሉ የማድረግ ግብ እንዳለውም ተናግረዋል።

በመግባቢያ ሰነድ ፊርማው ላይ ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ በበኩላቸው "ከአሜሪካ የትምህርት ተቋም አጋራችን ጋር በመስራታችን ደስተኞች ነን" ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለውም "ለፕሮጀክቱ ምርታማነትና ለስኬታማነቱ ያላሰለሰ ጥረት የሚደረግ ሲሆን የምህንድስናውን የትምህርት ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል" ብለዋል።

ሚስተር ኩይ ሮሙ በበኩላቸው ጅማ ዩኒቨርሲቲና የቴክሳሱ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመጣጣኝና አቻ ተቋሞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሁለቱም ተቋማት በሰልጣኝ ተማሪዎች ብዛትና በትምህርት መርሃ ግብሮች ተመሳሳይነት ያሏቸው ናቸው።

ሁለቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያደረጉት ስምምነት በሃገራችን የምህንድስና ትምህርት ስልጠና ዘርፍን የተሻለ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሆነም ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም