የኢንዱስትሪውን አፈፃፀም ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል

62
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋለውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2011 ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው። ኢትዮጵያ በ2012 መጨረሻ የማምረቻ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ መጠንን 3 ነጥብ 57 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ያቀደች ሲሆን እስከ አሁን ያለው አፈጻጸም 436 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል። ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን እንዳሉት የማምረቻ ኢንዱስትሪው በተለያዩ ችግሮች የታጠረ በመሆኑ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በቅንጅት መሥራት ይገባል። በዘርፉ አፈጻጸም ላይ ከሚታዩ በርካታ ችግሮች መካከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪው ከመሰማራት ይልቅ በቀላሉ ብዙ ትርፍ በሚያገኙበት የአገልግሎትና የንግድ ዘርፍ ላይ ማተኮራቸው ዘርፉ ዕድገት እንዳይታይበት አድርጎታል። በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለማስወገድና ባለሃብቶች በኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። በሥራ ላይ ያሉ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሃ-ግብር እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል። የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የኢንዱስትሪ ክላስተር መጠቀም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ዶክተር አምባቸው ጠቁመዋል። ከክልሎች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በእውቀትና ክህሎት ላይ ያለውን ችግር ለማስወገድ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም