በሰሜን ሸዋ ዞን በሃሰት የመሰክሩ 35 ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

106
ደብረብርሃን ግንቦት 8/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግለሰቦችን ለመወንጀል በሃሰት የመሰክሩ 35 ግለሰቦች እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አጣለ ዶሰኛ ለኢዜአ እንደገለጹት ሃሰተኛ ምስክር መስጠት የፍትህ ስርዓቱን በማዛባት ክፉኛ እየጎዳው ነው። ችግሩን ለመቅረፍ የሕብረተቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለፍትህ ስርዓቱ መጎልበት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። "ከህብረተሰቡ በሚደርስ ጥቆማና በመስቀለኛ ጥያቄዎች የሀሰተኛ ምስክር ቁጥርን ለመቀነስ ጥረት ቢደረግም አንዳንድ ግለሰቦች አሁንም ሆን ብለው ተማክረውና ተደራጅተው በመመስከር ግለሰቦች ያለጥፋታቸው እንዲቀጡ እያደረጉ ነው" ብለዋል። በዚህ ዓመት ሃሰተኛ ምስክሮችን በተደራጀ አግባብ ለመያዝ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር 35 ግለሰቦች በሃሰት ሲመሰክሩ ተይዘው ከ6 ወር እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል። የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ማኔጅመንት በሁሉም ወረዳ ፍርድ ቤቶች በመንቀሳቀስና የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ፍትህ እንዳይዛባ ለማድረግ አተኩሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የፍርድ ቤት ዳኞች የቀርበላቸውን የሰነድና የሰው ማስረጃ ተንተርሰው ውሳኔ ስለሚሰጡ ፍትህ እንዳይዛባና አጥፊም እንዲታረም ህብረተሰቡ፣ የሃይማቶት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ሃሰተኛ ምስክሮችን በማጋለጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ገዙ አሸኔ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ በህገ-ወጥ ደላሎችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ሳይታለል ሃሳቡን በትክክለኛ መረጃ አስደግፎ ለፍርድ ቤት በማቅረብ የራሱን መብት ራሱ ማስከበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ "የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብ ላይ ተገቢና አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ከእንደእዚህ አይነት ድርጊት ራሱን ሊጠብቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ በወረዳው መሬት ለመውረስ ያልሞተውን ግለሰብ ሞተ ብለው በሀሰት በመሰከሩና አስገድዶ ያልደፈረውን ወጣት እሱ ነው የደፈራት ብለው በመመስከር ፍትህን ባጓደሉ 3 ግለሰቦች ላይ ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት እስራት እንዲቀጡ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ የአንጾኪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ዘላለም አዱኛ በበኩላቸው "አንዳንድ ግለሰቦች የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት እርስ በእርስ በመደራጀትና ለዳኛው ብር እንሰጣለን" በሚል የሚያጭበረብሩ መኖራቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ፍትህ እንዳይዛባ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም