የትምህርት ተቋማትንና ትምህርት ፈላጊዎችን የሚያገናኝ ኤግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

77
አዲስ አበባ ነሃሴ 10/2010 በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የትምህርት ተቋማትና ትምህርት ፈላጊ ተማሪዎችን በአንድ ላይ የሚያገናኝ ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው። ኤግዚብሽኑን  ለሚጎበኙ 100 ተማሪዎች በዕጣ ነጻ የትምህርት ዕድል የሚሰጥ ይሆናልም ተብሏል። 'ኒው አይሲቲ እና ኢቨንት ኦርጋናይዘር' እና 'ሰላም ሄልዝ ኮንሰልታንሲ' በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የትምህርት ተቋማትና ትምህርት ፈላጊ ተማሪዎችን በአንድ ላይ ለማገናኘት ያለመ ኤግዚቢሽን ከነሃሴ 25 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ይካሄዳል። የኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች እንዳሉት ኤግዚብሽኑን ለሚጎበኙ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በዕጣ ነጻ የትምህርት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን ከፍለው መማር ላልቻሉ ዜጎች ዕድል ይሰጣል። ኤግዚቢሽኑ ተማሪዎችን ከትምህርት ተቋማት ጋር ከማገናኘት ባለፈ ፍላጎታቸውንና አቅማቸውን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የሚፈልጉትን ስልጠና ለመረዳትና ለመወሰን እንደሚያግዝ የሰላም ሄልዝ ኮንሰልታንሲ ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ቱሉ ተናግረዋል። ኤግዚቢሽኑ በአገሪቱ ላይ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡትን የትምህርት ወይም የስልጠና ዓይነቶችን በዝርዝር እንዲያስተዋውቁና ተማሪዎችም የሚማሩትን የትምህርት መስክ በማወቅ ተመዝግበው እንዲማሩ ለማድረግ ያግዛልም ብለዋል። በኤግዚቢሽኑ ላይ ማንኛውም በመደበኛም፣ በቀንም፣በማታም ወይም በርቀት የስልጠና መርሃ ግብር አጫጭር ስልጠና የሚሰጡ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። በኤግዚቢሽኑ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሚያስተምሩት ትምህርት አጭር ገለጻ ያደርጋሉ ብለዋል። ተማሪዎች፣ ወላጆችና ትምህርታቸውን ማሻሻል የሚፈልጉ ዜጎች ሊማሩ ወይም ሊሰለጥኑ ያሰቡትን የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሳያውቁና ሳይመርጡ ከመማር ይታደጋቸዋል ብለዋል። የኤግዚቢሽኑ መግቢያ በነጻ ሲሆን ከነሃሴ 25 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም