በሱማሌ ክልል የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

2363

ጅግጅጋ ነሀሴ 10/2010 በሱማሌ ክልል የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት በመቃወምና በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።

ሰላማዊ ሰልፉን የዞኑ ተወላጅ ምሁራን ያስተባበሩት ሲሆን በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ሁከት የሚያወግዙ መፈክሮች ተንፀባርቀውበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይዘውት የመጡት የመደመር  እሳቤም በሰልፉ ድጋፍ አግኝቷል።

ሰልፉን ካስተባበሩት ምሁራን አባል አቶ ቡሌት መሀመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሁከቱን የፈጠሩ አካላት የሱማሌ ማህበረሰብን የማይወክሉና የዜጎችን አብሮነት የሚቃወሙ ናቸው።

መንግስት ሁከቱን ያቀነባበሩና እጃቸው ያለበትን አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለፍርድ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከሰልፉ ባሻገር በሁከቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ አድርገዋል።

እንደ አቶ ቡሌት ገለፃ ምሁራኑ በሁከት ጉዳት የደረሰበት የአካባቢው ቤተክርስቲያን የሚታደስበትን ሁኔታን በሚመለከት ውይይት ያደርጋሉ።