በጎርፍና በመሬት መንሸራተት የ51 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል-የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን

68
አዲስ አበባ  ነሐሴ 10/2010 በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰተ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የ51 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። ክረምቱ እስከሚጠናቀቅ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ሕብረተሰቡ ራሱን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ አሳስቧል። ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ዳመና ዳሮታ የጎርፍ አደጋ ስጋትን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከበልግ ወቅት መጨረሻ ጀምሮ በታየው ከፍተኛ እርጥበትና ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ  ሳቢያ በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት ታይቶባቸዋል። ከባለፈው ግንቦት  እስከ ሐምሌ  መጨረሻ በተሰበሰበው መረጃ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 111 ወረዳዎች በጎርፍ አደጋ የተጠቁ ሲሆን 12 ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት ገጥሟቸዋል። በዚህም 24 ሺህ 232 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ለህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑንም አቶ ዳመና ተናግረዋል። በአምስት ትምህርት ቤቶችና በ17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በጎርፍ አደጋ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል። በቀጣይም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አብዛኛው ክፍል እንዲሁም የትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ለቅጽበታዊ ጎርፍ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑንም ጠቁመዋል። በተለይ በአዋሽ፣ በባሮ አኮቦና በአባይ ተፈሰስ አንዳንድ አካባቢዎች በወንዝ ሙላት ሊጠቁ ይችላሉ ብለዋል። በጎርፍ ሳቢያ ውሃ ወለድ በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኮሚሽኑ አሳስቧል። በቀጣይ ህብረተሰቡ ለጎርፍ መከላከያ የተሰሩ የውሃ ማገጃ መጠገንና ማጠናከር፣ በወንዝና ወንዝ ዳርቻዎች ላሉ ህብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት፣ የጎርፍ ማስወገጃ ቦዮችን መጥረግና በማሳ ዙሪያ የጎርፍ መከላከያ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ኮሚሽኑ የጎርፍ መከላከል ግብረ-ሃይል በማቋቋምና የጎርፍ መጠባበቂያ ፕላን አዘጋጅቶ በመስራት ላይ ሲሆን ጉዳቱ ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም