አዲሱ ካቢኔ ኀብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት-ነዋሪዎች

48
አዲስ አበባ ነሃሴ10/2010 አዲስ የተመረጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ኀብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጠየቁ። በከተማዋ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመሠረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትና የሥራ አጥነት ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባም በአጽንኦት ያነሳሉ ነዋሪዎቹ ። በከተማ አስተዳደሩ የተደረገው አዲስ የካቢኔ ሹመት በኢትዮጵያ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አንዱ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድም ገልጸዋል። በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው በመሆኑ አዲሱ ካቢኔ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ለውጡን ተግባራዊ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። አቶ ደረጀ በቀለ”የመሬት ፖሊሲው በጣም የጠበቀ እና ዜጎችን ተጠቃሚ የማያደርግ ነው ማለት ይቻላል። አንድ ሰው መኖሪያ ቤት ቢፈልግ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቦ የመመዝገቢያ እድሉም የተወሰነ ነው ከዚያም በኋላ የመጠበቁ እድል በጣም ረጅም ዘመን ነው እንደገና ደግሞ በዚያ ዓይነት የቤት ፍላጎትን ማዳረስ አይቻልም። ፈርሰው ለብዙ ዘመን ልማት ላይ ያልዋሉ ቦታዎች መፍትሄ ቢያገኙ።”ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ  ያለውን ብዙ ስራ ፈላጊ  ከመድረስ አንጻር “ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል” ያሉት ደግሞ አቶ ሬድዋን ምትኩ ናቸው፡፡ አቶ ሙሉጌታ ስብሃት በበኩላቸው የካቢኔ ለውጡ እስከ ወረዳ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው አዲሱ የከተማ ካቢኔ ህዝቡን ለምሬት የዳረጉ የመንገድና የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍ መስራት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ካቢኔው ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ኀብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በተለይም ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከአዲሱ አመራር ጎን በመቆም አስተዋጽኦ የማድረግ የዜግነት ግዴታ እንዳለበት ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በከተማ ደረጃ ያሉ አመራሮችን በአዲስ አዋቅሮ የለውጥ ሥራውን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም