አርሶ አደሩ አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ ጎን ለጎን የግብርና ስራውን ማጠናከር አለበት

86

ደሴ መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) አርሶ አደሩ አካባቢውን ከህውሃት አሸባሪ ቡድን ነቅቶ ከመጠበቅ ባለፈ ለሃሰተኛ መረጃዎች ትኩረት ባለመስጠት የግብርና ስራው ላይ ማተኮር እንዳለበት የደቡብ እዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል አለሙ አየነ ተናገሩ።

በደቡብ ወሎ ዞን የጊምባና አቀስታ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለጋምቦ ወረዳ በወሎ ግንባር ደላንታ ተገኝተው ለስራዊቱ  ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ብርጋዴል ጀነራሉ በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንዳሉት አሸባሪው የህወሃት ቡድን ያደገበትን የሃሰት ወሬ በመንዛት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ስራውን እንዳይከውን ጥረት እያደረገ ነው።

"እንደ ቡድኑ እቅድና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ቢሆን እስከ አሁን አዲስ አበባ ገብቶ አገሪቱን በተቆጣጠረ ነበር" ያሉት ምክትል አዛዡ አርሶ አደሩ አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥመው ለፀጥታ መዋቅሩ መጠቆምና ለግብርና ስራው ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ከስራዊቱ ጎን ተሰልፎ በሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍም ድል እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመው፤ "ቅንጅታችንንና አንድነታችንን አጠናክረን በማስቀጠል የመጨረሻውን ድል የምንሰማበት ቀን ሩቅ አይሆንም" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁሉም በየተሰማራበት የሙያ መስክ ጠንክሮ በመስራት ውጤታማ መሆን አለበት” ያሉት ምክትል አዛዡ ጊምባና አቅስታ ከተማ አስተዳደሮችና ለጋምቦ ወረዳ ግንባር ተገኝተው ላደረጉት ድጋፍና ደጀንነት አመስግነዋል፡፡

የጊምባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አንዋር እሸቴ በበኩላቸው "አሸባሪውን ቡድን ዳግም ስጋት በማይሆን መልኩ ለመቅበር አካባቢያችንን በመጠበቅ አንድነታችንን እናጠናክራለን" ብለዋል።

"የቡድኑ እድሜ እንዲያጥርና የህዝብ ሰቆቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ስራዊቱን በምንችለው አቅም በመደገፍ ደጀንነታን በተግባር መግለጽ የግድ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የከተማው ህዝብ ከለጋምቦ ወረዳና አቀስታ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ከ725 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 15 ሰንጋና 81 የበግ ሙክት ለስራዊቱ ግንባር ተገኝቶ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

"ግንባር ተገኝተን ስራዊቱን በማየታችንና ደጀንነታችንን በተግባር በመግለጻችን ተደስተናል" ያሉት ከንቲባው ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የለጋምቦ ወረዳ ተወካይ ወይዘሮ መዝገበ ስጦት በበኩላቸው እንደተናገሩት ለመከላከያ ስራዊት፤ ለልዩ ኃይሉና ፀጥታ አባላት 27 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ አሁን 8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡ ተችሏል።

ከዚህ በፊት 100 ኩንታል ደረቅ ሬሽን ምግብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው፤ "ህብረተሰቡን በማስተባበር የምናደርገው ሁለተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በወሎ ግንባር ደላንታ በተደረገው የድጋፍ ስነ-ስርዓት ላይ የደቡብ ወሎ ዞንና የወረዳ አመራሮች የስራዊት አባላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም