ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ዳይሬክቶሬት ይቋቋማል…የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

64
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራና ያሉባቸውን ችግሮች ሊፈታ የሚችል ዳይሬክቶሬት ሊያቋቋም መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን የ2010 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል አከባበር ላይ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የእውቅናና ምስጋና ስነ ስርዓት አካሄዷል። በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም እንደተናገሩት "ህብረተሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው" በዚህም ሳቢያ አካል ጉዳተኞች  በስራ እድልና አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ ችግር ይገጥማቸዋል። መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ለማስከበር እንዲሁም ሁለንተናዊ ተሳትፏአቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ። የተለያዩ ህግጋት መውጣታቸውን፣ የልማትና የለውጥ ፖሊሲዎች መነደፋቸውንና አስፈፃሚ አካላትን በማደራጀት ከባለድርሻ አካላትና ማህበራት ጋር መሰራታቸውን ለአብነት ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቷአቸዋል የሚለውን ስናይ ረጅም ርቀት መጓዝ እንዳለብን ይጠቁማል ያሉት ሚኒስትሯ  አካል ጉዳተኞችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግና የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትም አንድ አካል በመስሪያ ቤታቸው በዳይሬክቶሬት ደረጃ ለማቋቋም ጥናት መጠናቀቁን ገልፀዋል። የጥናቱ ውጤት ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር መላኩን የገለፁት ዶክተር ሂሩት ፤ፍቃዱ እንደተገኘም ዳይሬክቶሬቱ በሚኒስቴሩ ይቋቋማል ብለዋል። አካል ጉዳተኞች የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አካታች ስርዓት ሊኖር ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ዳይሬክቶሬቱ በሁሉም ተቋማት የሚደራጅ እንደሚሆንም ነው የገለፁት። በሀገሪቱ ለአካል ጉዳተኞች የግንዛቤ ማነስና የፖሊሲዎችና ማዕቀፎች ክፍተት መኖሩን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው። ሚኒስቴሩ ለአካል ጎዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ክፍል ቢያቋቁም በጋራ ለመስራት የሚጠቅም እንደሆነም ነው አቶ አባይነሀ የገለፁት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም