የሽብር ተግባሩን አገራዊ ለማድረግ ሲሰራ የቆየው አሸባሪው ህወሃት እርስ በርሱ እየተጠፋፋ ነው

57

መስከረም 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪነት ተግባሩን አገራዊ ለማድረግ ሲሰራ የቆየው አሸባሪው ህወሃት መዋቅሩ ፈራርሶ እርስ በርሱ እየተጠፋፋ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሴ ገለጹ።

አቶ ተሻለ ንጉሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ አሸባሪው ሕወሃት ለ27 ዓመት ሲያደርገው የቆየውን መንግስታዊ ሽብር በትግራይ ህዝብ ላይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ፈጽሞታል።

ከመንግስትነት ወደ ሽፍትነት የተለወጠው ቡድኑ "የሽብር ተግባሩን ወደ አማራና አፋር ክልሎች በማስፋት ንጹሃንን ጨፍጭፏል፤ ንብረት አወድሟል፤ እንስሳትን ሳይቀር ረሽኗል" ብለዋል።

የትግራይ ህጻናትን በጭነት መኪና እየጫነ እሳት ውስጥ ከመማገዱ በላይ "የአማራን ህዝብ ከህጻናት እስከ አረጋውያን በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በርሀብና በሽታ እንዲሰቃዩ በማድረግ የመኖር ሕልውናቸው ስጋት ሆኗል" ብለዋል።

ይህም ጦርነቱንና የሽብር ተግባሩን አገራዊ ለማድረግ ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር በመተባበር ሲሰራ መቆየቱን እንደሚያሳይ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ህዝብ በተሰነዘረበት የመልስ ምት ከአፋር ክልል ተደምስሶ መውጣቱን ያስታወሱት አቶ ተሻለ፤ በሌሎች ግንባሮችም መመታቱንና አቅሙ እየተዳከመ መዋቅሩ እየፈረሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

"አሸባሪ ሕወሃት በታሪኩ እርስ በርሱ እየተበላላ የመጣ" መሆኑን ገልጸው፤  ዛሬም በእርጅና ላይ ሆኖ በስልጣን፣ ዝናና እና ጥቅም ሽኩቻ እየተጠፋፋ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የቡድኑ አብዛኞቹ አመራሮች መደመሰሳቸውንና የሀብት ምንጮቹ መድረቃቸውን ተከትሎ ስትራቴጂክ አመራር እንደሌለው ገልጸዋል።

የአሸባሪው ሕወሃት መዋቅር በመፈራረሱ ራሱም ሆነ በራሱ አምሳያ የፈጠራቸው ስብስቦች ስትራቴጂክ ስጋት እንዳልሆኑ አቶ ተሻለ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙሃን ስለአሸባሪው ህወሃት የሽብር ተግባር ህዝብን ሊያሳውቁና ሊያስገነዘቡ የሚችሉ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም