የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2011 ትምህርት ዘመን አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

130
ደሴ ነሀሴ 10/2010 የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2011 ትምህርት ዘመን ለማስተማር የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር አስታወቀ። በማህበሩ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአባላት ልማት በጎ ፈቃድ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ሰውነት እንዳሉት አዳሪ ትምህርት ቤቱ የተገነባው በ2002 ዓ.ም በተካሄደው የአልማ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ በተገነባው ቃል መሰረት ነው። በወቅቱ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ የፍሊንት ኢስትውድ ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማህበር ባለቤት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት ቃል መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚሁ መሠረት አክሲዮን ማህበሩ በወቅቱ በገባው ቃል መሰረት የአዳሪ ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለማስረከብ ከ29 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤቱን በተሟላ መልኩ ስራ ለማስጀመር አማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና ግብዓቶች የማሟላት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደርም በ5 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት የግንባታ ቦታ በማዘጋጀት፣ ከይዞታቸው ለተነሱ ሰዎች የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ በመስጠት እንዲሁም ለግንባታው የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማቶችን በማሟላት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ፕሮጀክት ስራአስኪያጅ አቶ ናትናኤል ደሳለኝ በበኩላቸው አደሪ ትምህርት ቤቱ በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱን አውስተዋል። በየጊዜው እየናረ በመጣው የግንባታ ዋጋ ምክንያት ግንባታው ቢጓተትም በወቅቱ ከተያዘለት በጀት በተጨማሪ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ አሁን ለይ ለማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል። አዳሪ ትምህርት ቤቱ የቢሮ፣ የመሰብሰቢያና የመመገቢያ አዳራሾችን፣ የመማሪያና የማደሪያ ህንጻዎችን፣ የቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራ ክፍሎችን ያካተተ 13 ህንጻዎችን የያዘ ነው። ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችም ተዘጋጅተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሰርአተ ትምህርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሽብሬ ጆርጋ በበኩላቸው በክልሉ የመጀመሪያው የሆነው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ውጤታማ እንዲሆን በቦርድ እንዲተዳደር ይደረጋል፡፡ ቢሮው መምህራንን ከመመደብ ጀምሮ አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ በ2011 የትምህርት ዘመን አንድ መቶ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን በመቀበል ስራውን እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚገቡ ተማሪዎችም የላቀ ውጤት ያላቸው፣ በልዩ ክህሎታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመረጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችን ለመቀበልም ዝርዝር መስፈርቶችን በማውጣት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው  “የስምንተኛ ክፍል ውጤት፣ የቤተሰብ ፍላጎት፣ የተማሪዎች ልዩ ተሰጥኦና ባህሪ ከመስፈርቱ ውስጥ ይካተታሉ'' ብለዋል። “አንድ ሆነን እንደ ሺህ፤ሺህ ሆነን እንደ አንድ!” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው አልማ 2002 ቴሌቶን አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ቃል መገባቱ የሚታወስ ነው፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም