በጎንደር ማራኪ ክፍለ ከተማ ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ተያዘ

53

ጎንደር ሚያዚያ 22/2010 በጎንደር ማራኪ ክፍለ ከተማ ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መያዙን  ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በጎንደር ከተማ የ3ኛ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የማራኪ ክፍለ ከተማ ኮማንድ ፖስት አባል ዋና ኢንስፔክተር ስማቸው ደምሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጦር መሳሪያና ጥይቶቹ የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 18 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችን ጨምሮ 2ሺ 495 የክላሽና  4ሺ 266 የመትረየስ ጥይቶች ተይዘዋል፡፡ የጦር መሳሪያውን ደብቀዋል የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝውውር የሚሳተፉ ግለሰቦችን በማጋለጥና ህግ ፊት በማቅረብ በኩል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም