አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ከምንም በላይ ሰላምን ለማስፈን መስራት አለበት

64

መስከረም 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ሰላም ከሌለ የምንፈልገውን ልማት ማሳካት ስለ ማይቻል የሚመሰረተው መንግሥት ከምንም በላይ ሰላምን ለማስፈን መስራት አለበት” ሲሉ የሐይማኖት አባቶች አመለከቱ።

የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመሠረተው መንግሥት የታችኛው ማኅበረሰብ ጋር ዝቅ ብሎ መሥራት እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።

የ2014 የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተከበረ ይገኛል።

በዚህ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሐይማኖት አባቶች መስቀል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሰላምን የሰጠበት ነው ብለዋል።

የደብረ ፀሐይ ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዐከ ኃይል ቀሲስ ቀለመወርቅ አሰፋ “የሚያስፈልጉንን ስኬቶች ለማስመዝገብ ሰላም መሠረታዊ ነገር ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም ቀድሞ የነበረውን ሰላምና አንድነት ለማስቀጠል አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት መስራት ይኖርበታል ፤ ይህንንም ለማሳካት የታችኛው የማኅበረሰብ ክፍልን ማየትና በዕቅዱ ውስጥ አካቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ነው ያሉት።

አክለውም ችግሮች ሲከሰቱ ቀድሞ ተጎጂ የሚሆነው የታችኛው ማኅበረሰብ በመሆኑ ቀጣይ የሚመሠረተው መንግስት የሚያከናውናቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እነሱን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ሲሉ አመላክተዋል።

የደብረ መዊዕ ቄሰ ገበዝ መልዐከ ብርሃን ቀሲስ ተቋም ማዕቶት በበኩላቸው ክርስትያኖች በክርስቶስ ያገኘነውን ሰላም ተግባራዊ ልናደርገው ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸው፤ “ይህ ካልሆነ  ስማችን ከተግባራችን ጋር አይሄድም ስማችን ከተግባራችን ጋር እንዲሄድ ለሰላም ዋጋ ሰጥተን ልንሰራ ይገባል” ብለዋል።

“መንግስት ሰላምን ለማስፈን ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ያስፈልጋል፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ዘወትር እንደምታደርገው ሰላምን  በሚመለከት ታስተምራለች ከመንግሥት ጎን ሆና ትሰራለች" ሲሉ ገልጸዋል።

ሰላም ከሌለ የምንፈልገውን ልማት ማሳካት፤ ዕቅዶቻችንን ተግባራዊ ማድረግ እና የተበላሹ ነገሮችን ማስተካከል ስለ ማይቻል አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከምንም በላይ ሰላምን ለማስፈን መስራት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም