በአገራዊ ማንነትና በብሄር ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖር በቀጣይ ትኩረት ይደረጋል

83

አዲስ አበባ፣  መስከረም 16/2014 ( ኢዜአ) በአገራዊ ማንነትና የብሄር ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖር በቀጣይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሕግ አማካሪ ዶክተር ዘለቀ ተመስገን፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በቀጣዮቹ ዓመታት የፖለቲካ ውዝግብ እንዲፈጠርባቸው የተሰሩ ነገሮችን የማስተካከል ስራ ትኩረት ይደረጋል።

ከእነዚህ መካከል በተለይም በአገራዊ ማንነትና የብሄር ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖር ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባለብዙ ማንነት እና ብዝሃ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የበርካታ ባህሎችና ትውፊቶች ጅረት የሚፈስባት አገር በመሆኗ የእያንዳንዱ ዜጋ መገለጫዎችና የኢትዮጵያ እምቅ ሃብቶች መሆናቸውን በቅጡ ማስገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አንደነት እና የብሄር ማንነት ሚዛናቸው ተጠብቆ እንዲዘልቅ መስራት የቀጣይ የቤት ስራ መሆን እንዳለበት ዶክተር ዘለቀ ገልጸዋል።

በአገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶችን በማስተናገድ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲጎለብት ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።

በአገራዊ አንድነት ዙሪያ የሌሎች አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ለኢትዮጵያ በሚመች መልኩ ለመተግበር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አዲስ በሚመሰረተው መንግስት በተለያዩ እርከኖች ህዝብን ማዕከል አድርገው የሚያገለግሉ፤ በአገራዊ አንድነትና ሉአላዊነት ዙሪያ በትኩረት የሚሰሩ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት አምስት አመታት በግልም ይሁን በቡድን የመንግስት በትረ ስልጣን የሚይዙ አካላት ለሀገሪቱ ሰላም፣ ለሕዝቦች ደሕንነትና ለጋራ እድገት የሚሰሩ ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት።


በምክር ቤት መቀመጫ የሚኖራቸው ተወካዮች የሕዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንዲሁም የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ የመንግስት ምስረታ ሂደት የፌደራል መንግስቱ ሁለቱ ምክር ቤቶች የስራ ዘመናቸውን የሚጀምሩት በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት አዲሱ የመንግስት ምስረታ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም