አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኮንጎ ሪፐብሊክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረቡ

103
አዲስ አበባ ነሐሴ 10/2010 በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኮንጎ ሪፐብሊክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ክሎድ ጋኮሶ አቀረቡ። አምባሳደር ሉሊትና የኮንጎ ሪፐብሊክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም አመታት የቆየውን መልካም ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎችና በክልላዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። አምባሳደር ሉሊት በሩዋንዳ ሆነው ኢትዮጵያ ከኮንጎ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚሸፍኑ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አምባሳደሯ ለሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፓል ካጋሜ ባለፈው ጥር 2010 ዓ.ም የሹመት ደብዳቤያቸውን በማቅረብ በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ኮንጎ ሪፐብሊክ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያ ከኮንጎ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ግንኙነት ሩዋንዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ትሸፍናለች።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም