በተማርነው ሙያ ህዝባችንና ሀገራችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን

69

ነቀምቴ፤ መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) በተመረቁበት ሙያ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለ16ኛ ጊዜ  ምዕራፍ ሁለት በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች 788 ተማሪዎችን ዛሬ በመጀመሪያና ሶስተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡

ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል በኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ተመራቂና የሜዳለያ ተሸላሚ ተማሪ ደራርቱ ተስፋዬ ፤ ጠንክራ በመስራቷ ለሜዳሊያ ሽልማት መብቃቷ እንዳስደሰታት ገልፃለች።

ስራ ጠባቂ ሳትሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን ራሷን፣ ሕብረተሰቡንና ሀገራን በታማኝነት  ለማገልግል መዘጋጀቷን ነው ለኢዜአ የተናገረችው፡፡

የግብርና ኢንጂነሪንግ ተመራቂና የሜዳለያ ተሸላሚ ሽብሩ ሀብታሙ በበኩሉ፤ ጠንክሮ መስራቱ ለሽልማት እንዳበቃው ጠቅሶ፤  በተማረው ሙያ የሕብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ከሻምቡ ካምፓስ የሶስተኛ ዲግሪ ተማራቂ ደሣለኝ ነጋሣ ፤  ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ለመመረቅ መብቃቱን አመልክቶ፤  በምርምር  የተለያዩ  የቲማቲም ዝርያዎች ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

በምርምር ያገኟቸው የቲማቲም ዝርያዎች በሽታን ለመቋቋም የሚችሉና ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ በማዳረስ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚጥር አስታውቀዋል፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ እንደገለጹት፤ ከተመረቁት 788 ተመራቂዎች መካከል786 የኢንጂነሪንግ ሰልጣኞች  ሲሆኑ ቀሪዎቹ በተፈጥሮና ኮምፒዩቴሽናል ሳይንስ እና በፕላንት ሳይንስ በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታውን ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

ተመቂዎቹ በተማሩት ሙያ ህብረተሰቡንና ሀገራቸውን በቅንነት ከማገልገል ጎንለጎን አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በሌሎችም የበጎ ተግባር ስራ ላይ እንዲሳተፉ አበረታተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ የ"ኤም.ኤች.ኮንሰልቲንግ" ባለቤት ዶክተር ኢንጂነር መሠለ ኃይሌ፤ ተመራቂ ተማሪዎች የመንግስት ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ በተመረቁበት ሙያ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መክረዋል።

በዚህም ራሳቸውን በመቻል ሀገራቸውንና ሕዝቡን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ከወዲሁ ራሳቸውን በማሳመን ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም