አዲሱ መንግሥት በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል

64

መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ሊኖረው እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ገለጹ።

በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ማሸነፉን ያረጋገጠው ፓርቲ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ መንግሥት ይመሰርታል።

አዲሱ መንግስት ሊከተላቸው ስለሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች፣ መጪው አገራዊ ተስፋና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል።

ዶክተር ደመቀ እንዳሉት፤ መራጩ ህዝብ ከአዲሱ መንግስት በሁሉም መስኮች በርካታ ለውጦችን ይጠብቃል።

በተለይ ባለፉት ሥርዓቶች የተበላሹትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ አቅጣጫዎችን በመቀየስ "የተለያዩ ተግባራት ያከናውናል" የሚል እምነት አላቸው።

በተለይም አዲሱ መንግሥት ከፖለቲካ ውግንና ይልቅ እውነተኛ የህዝብ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ሰዎች በመምረጥ የቀረጻቸውን ፖሊሲዎች ወደ ተግባር መለወጥ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

እንደ ዶክተር ደመቀ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ ከፍ በማለቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን በመከለስ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

"ለወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ የሚሰራበት እንደሚሆን ተስፋ" አለኝ ያሉት ምሁሩ፤ አዲሱ መንግስት የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት፣ ሰላምን ማረጋገጥና በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ነው ያመለከቱት።

ህዝቡ በምርጫው ወቅት ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ተቋማትን መገንባት ላይ እንዲሁ በሰፊው ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ጠቁመው፤ ሆኖም በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች፣ ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና ሞት የተስተዋለበት በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሄድ ማድረጉን ተናግረዋል።

"በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከህዝቡ ድጋፍ ጋር ተያይዞ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ እምነት አለኝ ነው" ያሉት።

በኢትዮጵያ የተካሄደው ስድስተኛው ምርጫ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች በአንጻራዊነት የተሻለ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ዶክተር ደመቀ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም "ህዝቡ በራሱ ፈቃድ አገር የማዳን ጉዳይ ነው" ብሎ በተለይም በአዲስ አበባ እስከ ለሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ "ይበጀኛል" ያለውን መምረጡን ያነሳሉ።

"የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻ ሆኖ ምርጫው እንዲካሄድ ማድረጉ የተለየ ምርጫ ያደርገዋል" ያሉት ምሁሩ፤ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና ድህረ ምርጫዎች ምንም ዓይነት ግጭት ሳይኖር መካሄዱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"በውጭ አገር ኢትዮጵያ ልትበጠበጥ ትችላለች፣ ምርጫው ሊበላሽ ይችላል" ብለው ያሰቡ እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር ደመቀ፤ በተቃራኒው ግን ህዝቡ ሰላማዊ ምርጫ ያደረገበት እንደሆነ አስታውሰዋል።

ከቁሳቁስ ጋር በተያያዘና በአንዳንድ ቦታዎች የፓርቲዎች ቅሬታ ቢኖርም "ከሞላ ጎደል ህዝብ የዲሞክራሲ ልምምድ ሙከራ ያደረገበት ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን "የሽግግር መንግሥት አያስፈልግም" በማለት ምርጫ ማካሄዳቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸው፤ "አሁን ባለው ሁኔታ የሽግግር መንግሥት ስልጣን ለመከፋፈል ካልሆነ በስተቀር ህዝብ እንደመረጠው መንግሥት ልማትና ሰላም ያመጣል የሚል እምነት የለኝም" በማለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም