አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማክበር ይጠበቅበታል

102

መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለውና ለሕዝብ የገባውን ቃል ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ያከብራል ብለው እንደሚጠብቁ የሕግና የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊና ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ድምጹን ለሚፈልገው ፓርቲ ሰጥቶ አሸናፊው ፓርቲ መንግስት የመመስረቻው ዕለት ለመስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል።

የሕግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂ አቶ ሙክታር ኡስማን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተወዳደሩ ፓርቲዎች በተገቢው መልኩ የሕዝብ ድምጽ አግኝተዋል።

በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደው ምርጫ የሕዝብ ድምጽን ያገኘው ፓርቲ አዲስ መንግስት ሲመሰርት ለሕዝብ የገባውን ቃል "ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ያከብራል" ብለው እንደሚያምኑም አብራርተዋል።

አዲስ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ ሕዝቡን ከድህነትና ከኋላቀርነት የሚያወጡ ተግባራትን በማከናወን የገባውን ቃል በተግባር በማሳየት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ መሆኑን አስታውሰው፤ በተለይ በነጻነት የተካሄደውንና እንከን የሌለውን ምርጫ በማጣጣል ሕዝቡ በሚፈልገውና በመረጠው አካል እንዳይተዳደር ለማድረግ የጀመሯቸው  ጫናዎች ተገቢ አለመሆናቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ "ሕዝብ ይሆነኛል ያስተዳድረኛል" ያለውን ፖርቲ የመምረጥም ሆን ድምጽ የመስጠት መብት የራሱ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ፓርቲዎች ይህን ተገንዝበው ለሕዝቡ የገቡትን ቃል በተጨባጭ በመፈፀም የተሰጣቸውን እድል እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም የተካሔደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ "በሀገሪቷ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሕዝቡ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምጹን የሰጠበት እንደነበር ሁሉም የሚመሰክረው ነው" ያሉት ደግሞ የታሪክ ምሁራና የማህበረሰብ አንቂ አቶ ታዬ ቦጋለ ናቸው ።

ዘንድሮ የተካሔደው ምርጫ በአገሪቷ ዴሞክራሲ ስርዓትን ከማሳደግ ረገድ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው የገለጹት ።

በዚህ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ በአዲስ መልክ የሚመሰረተው መንግስት በሀገሪቷ ጉዳይ ላይ በየደረጃው ያሉ አካላትን በማሳተፍ እንድ እርምጃ ወደፊት መሔድ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

አዲስ መንግስት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ማንኛውም አካል የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር እንደሚገባውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም