ብልፅግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሃ ግብሩን በሐረሪ ክልል አካሄደ

64

ሐረር መስከረም 15 /2014 (ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ በቀጣዩ ሳምንት ለሚካሄደው ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ በሐረሪ ክልል አካሄደ።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ደጋፊዎችና አባላት ተገኝተዋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ኦርዲን በድሪ  እንደተናገሩት፤ብልጽግና ፓርቲ  ለወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት መረጋገጥ በሰጠው ልዩ ትኩረት ዕጩዎቹን ከነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አድርጓል።

"ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች እኩልና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ያስተናግዳል" ያሉት አቶ ኦርዲን፣ ፓርቲው በወንድማማችነት፣ በመተባበርና መቻቻል ያምናልም ሲሉ ገልጸዋል።

ፓርቲው ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱጀባር መሐመድ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂድ መቆየቱን ተናግረዋል።

ወጣት ሙና አብዲ ፤መራጮች የምርጫ ካርዳቸውን በአግባቡ በመጠቀም ድምጻቸውን እንዲሰጡበት መልዕክት አስተላልፋለች።

ምርጫው ሕዝቡ ይወክለኛል የሚለውን ፓርቲ የሚመርጥበትና ድምጹን የሚያሰማበት እንደሚሆን እምነቱን የገለጸው ደግሞ  ወጣት አቡበከር ዱሪ ነው።

የምርጫ ካርድ ወስዶ  ድምጽ ለመውጣት መዘጋጀቱን የተናገረው ወጣት አቡበከር፤ ሕዝቡም ይሆነኛል ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥም አመልክቷል።

ህዝቡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፏል።

በማጠቃለያ መድረኩ ላይም ዕጩዎች ትውውቅ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም