የአፋር አርብቶ አደርን የሰብል ልማት ለማሳደግ በምርምር የታገዘ ስራ እየተከናወነ ነው

126

ደሴ፣ መስከረም 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የጭፍራ አርብቶ አደሮች ውጤታማ የሰብል ልማት ስራዎችን እንዲያከናውኑ በምርምር የታገዘ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በጭፍራ ወረዳ ለአርብቶና አርሶ አደሮች ባቀረበው ምርጥ ዘር በመኸር የለማው ማሳ ትናንት ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ለሰብል ልማት ምቹ የሆነ መሬት ቢኖርም በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ብዙ መሬት ሳይለማ ጾም ያድራል።

ከግንዛቤ እጥረቱ ባሻገር የአፈር እርጥበት አለመኖር ችግር እንደሆነም ጠቁመዋል።

አብዛኛው ህብረተሰብ አርብቶ አደር ቢሆንም በተቆራረጠ መንገድም ጎን ለጎን ሰብል ለማምረት የሚሞክሩ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያም ጭምር ምርት እንዲያቀርቡብ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከሲሪንቃና ሰቆጣ የግብርና ምርምር ማዕከሎች ድርቅን መቋቋም የሚችሉ፣ የተሻለ ምርት የሚሰጡ፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን በስፋት ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተለይም የማሽላ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ ማሾና በቆሎ ሰብል ዘሮችን በማሰራጨት ለሌሎቹ ተሞክሮ እንዲሆን በ21 ሄክታር ማሳ በመኸር እንዲለማ መደረጉን አብራርተዋል።

መቀንጨርን ለመከላከል ከፍተኛ እገዛ የሚያደርገው የዳጉሳ ሰብል ከአካባቢው ጋር እንደሚስማማ ጠቁመዋል።

በሙከራ በአርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ማሳ የለማው የሰብል ቡቃያ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የጭፍራ ወረዳ እንሰሳት፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወግሪስ ሀፋ እንደተናገሩት፤ ከ5 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በእርጥበትና በግንዛቤ ክፍተት ማልማት የተቻለው 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያመጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ለቀጣይ ተስፋ የሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“የእርጥበት ማቆያ ዘዴዎችን በመተግበር ለሙከራ የተዘራውን ሰብል ውጤታማ ማድረግ ችለናል” ያሉት ኃለፊው፤ “ቀጣይ በእጥፍ ለማሳደግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተሻለ ቅንጅት ይሰራል” ብለዋል።

በጭፍራ ወረዳ የታአቦና ገሪሮ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጉድሬ ዳውድ በሰጡት አስተያየት ለእንሰሳት እርባታ እንጂ ለሰብል ልማት ብዙም ትኩረት ሰጥተውት እንደማያውቁ ጠቅሰዋል።

ባላቸው በቂ የእርሻ መሬት አልፎ አልፎ በቆሎና ማሽላ ለመዝራት ቢሞክሩም ውጤታማ ሆነው እንደማያውቁ አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን ዘር በመጠቀምና በተደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍ ሦስት ሄክታር መሬት በጤፍ፣ ማሽላና በቆሎ መሸፈን መቻላቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም