የተነቃቃውን የቱሪዝም ዘርፍ ውጤታማነት ለማስቀጠል ዘላቂ ሰላም ያስፈልጋል - ዶክተር ሂሩት ካሳው

83

ሀዋሳ፣ መስከረም 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገራዊ ለውጡ እየተነቃቃ የመጣውን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሰላም ግንባታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።

የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ "ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገት" በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል።

ሚኒስትሯ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት፤ ቱሪዝም ሥራ በመፍጠር የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ማህበራዊ መስተጋብርን በማሳለጥ ዓለምን ወደ አንድ መንደር በማምጣት ረገድ የጎላ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪዝም ሀብቶች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መጠበቅና ማልማት ከተቻለ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች እንደሚኖሩት አመልክተዋል።

ሃብቶቹ ተፈጥሮአዊ ባህሪያቸው ጠብቆ በማልማትና ለዓለም በማስተዋወቅ የህዝብን ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም ኃላፊቱን መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል።

“ዘርፉን በተፈለገው ልክ አልምቶ ለመጠቀም ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ ተግዳሮቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

''ሀገራችን መለያየትን ሳይሆን ፍቅርንና አንድነትን ትፈልጋለች፤ ለዚህ ፈተናና ተግዳሮት የሆኑ አካላትን በተባበረ ክንድ መጣል የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን'' ብለዋል።

የሲዳማ  ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ባለመመራቱ በቂ ጥቅም ሳያስገኝ መቆየቱን አንስተዋል።

መንግሥት ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የአሰራርና አመራር መዋቅር በመዘርጋት ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው ትኩረት እስከታች ድረስ እንዲወርድ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላት ሰላማዊ አካባቢን ለመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ለውጡ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ናቸው።

የኢትዮጵያ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ አጥላባቸው እንዳሉት፤ የቱሪዝም ቀን በክልሎች መከበሩ መስህቦችን ለማስተዋወቅ ይረዳል።

በዘርፉ ለረጅም ዓመታት የሰሩት የትራቭል ኢትዮጵያ አስጎበኚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሳምራዊት ሞገስ “መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በተሻለ ለመንቀሳቀስ አስችሏል” ብለዋል።

የሰላም እጦትና ጦርነት ተግዳሮት እንዳይሆን ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በበዓሉ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ የቱሪዝም አምባሳደር ሆነው ሲሾሙ ለቱሪዝም ዕድገት የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የዕውቅና የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም